AMN – ግንቦት 18/2018 ዓ.ም
በሰውነት ሕብረ ሕዋሳት ውስጥ ከልክ ያለፈ ፈሳሽ በሚከማችበት ጊዜ የሚከሰተው የእግር እብጠት በበርካታ ሰዎች ላይ የሚስተዋል የጤና እክል ነው።
ይህ ችግር በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች የሚገልጹ ሲሆን፣ መንስኤዎቹን መለየትና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባሉ።
እንደ ባለሙያዎች ገለጻ፣ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት እና ለረጅም ሰዓታት መቆም ወይም መቀመጥ ለችግሩ ዋነኛ ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ናቸው።
ከነዚህም በተጨማሪ የእድሜ መጨመር፣ እርግዝና፣ እንዲሁም የሥርዓተ-ምግብ (በተለይም የፕሮቲን) እጥረት ለእግር እብጠት መከሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።

ይሁን እንጂ እብጠቱ ከከባድ የጤና ችግሮች ማለትም ከስኳር፣ ከልብ፣ ከኩላሊት ወይም ከጉበት በሽታ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።
ይህንን ችግር በቤት ውስጥ ለመከላከልና እፎይታ ለማግኘት የሚረዱ ተፈጥሯዊ መፍትሄዎችም አሉ፡፡
ከነዚህም መካከል የደም ዝውውርን የሚያፋጥነው የውሃ ህክምና አንዱ ሲሆን፣ እግርን ለጥቂት ደቂቃዎች በሞቀ እና በቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ በማፈራረቅ መዘፍዘፍ ውጤታማ ነው።
በተጨማሪም እግርን ወደ ልብ አቅጣጫ በመጫን ማሸት (Massage) የተጠራቀመው ፈሳሽ እንዲሰራጭ ሲረዳ፣ የእንግሊዝ ጨው ደግሞ እብጠትንና ህመምን ለመቀነስ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

በሌላ በኩል እንደ ዝንጅብልና ሎሚ ያሉ ተፈጥሯዊ ግብዓቶች ጸረ-ብግነት ባህሪ ስላላቸውና መርዛማ ነገሮችን ከሰውነት ውስጥ ስለሚያስወግዱ፣ በሻይ መልክ መውሰድ መልካም መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
እነዚህ የቤት ውስጥ መፍትሄዎች እብጠቱ ቀላል በሆነ ጊዜ የሚረዱ ቢሆንም፣ ሁኔታው እየባሰ ከመጣ ወይም ከሌሎች ምልክቶች ጋር ከተያያዘ ግን በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ የባለሙያ ምክር ማግኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በበረከት ጌታቸው