ፓሪሰን ዠርማ ከ አርሰናል፦ ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ

AMN- ግንቦት 22/2018 ዓ.ም

የ2025/26 የውድድር ዘመን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዛሬ ፍፃሜውን ያገኛል። ፓሪሰን ዠርማ ከ አርሰናል ጋር የሚያደርጉት የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይከናወናል።

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ታሪክ ዘጠኝ ክለቦች ብቻ ምንም ሽንፈት ሳይገጥማቸው ዋንጫ አንስተዋል። አርሰናል ዛሬ ድል ከቀናው ይህን ታሪክ ይጋራል። የሰሜን ለንደኑ ክለብ የተመኘውን እንዳያገኝ ፊትለፊቱ የቆመው የባለፈው ዓመት የውድድሩ ባለድል ፓሪሰን ዠርማ ነው።

በሊውስ ኤነሪኬ እየተመራ ሌላ ከፍታ ላይ የደረሰው የፓሪሱ ክለብ ከስምንት ዓመት በፊት ሪያል ማድሪድ ካሳካው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ ለፍፃሜ የደረሰ ክለብ ሆኗል።

የዛሬ ተፋላሚዎች ባለፈው የውድድር ዓመት (2024/25) በግማሽ ፍፃሜ የመገናኘት ዕድል አግኝተዋል ፤ ፓሪሰን ዠርማ በኤምሬትስ 1ለ0 ፣ በፓርክ ደ ፕራንስ 2ለ1 በድምር ውጤት 3ለ1 በማሸነፍ ለፍፃሜ መብቃቱ ይታወሳል።

ሁለቱ ክለቦች የውድድሩ ጫፍ ላይ ለመድረስ የመጡበት መንገድ ተቃራኒ ነው። አርሰናል ጠጣር በሆነው የመከላከል ብቃቱ ታግዞ ፍፃሜ ደርሷል። የሚኬል አርቴታው ቡድን በሊግ ምዕራፍ ስምንቱንም ጨዋታዎች አሸንፎ የመጀመሪያው ክለብ ተብሎ ታሪክ ሲፃፍለት አራት ግቦች ብቻ ነበር የተቆጠሩበት።

ከባየር ሊቨርኩሰን ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን እና አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ባደረገው የደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይም ቢሆን የተመዘገበበት ሁለት ግብ ብቻ ነው።

ፓሪሰን ዠርማ በአንፃሩ ይበልጥ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ለዛሬው ፍፃሜ ደርሷል። የፈረንሳዩ ክለብ በአጠቃላይ 44 ግቦችን ተጋጣሚው ላይ አስቆጥሯል።

በተለይ ጆርጂያዊው የፊት መስመር ተጫዋች ክቪቻ ክቫራስኬሊያ ልዩነት ፈጣሪ ሆኗል። የቀድሞ የናፖሊ ተጫዋች 10 ግቦችን አስገኝቷል። ሰባቱን ግቦች ያስቆጠረው ከቼልሲ ፣ ሊቨርፑል እና ባየርን ሙኒክ ጋር በተደረጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ላይ ነው።

አርሰናል በሚኬል አርቴታ እየተመራ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ያሳየው መሻሻል በግልፅ ይታያል። በ2023/24 ሩብ ፍፃሜ የደረሰው ክለቡ ፣ በ2024/25 ደግሞ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ነበር ፤ ዘንድሮ ደግሞ ለፍፃሜ ደርሷል።

የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ የማንሳት ዕድል ያላገኘው አርሰናል ለፍፃሜ ሲደርስ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ከ20 ዓመት በፊት (በ2005/06) ለዋንጫ ቀርቦ በባርሰሎና 2ለ1 ተሸንፏል።

ፓሪሰን ዠርማም ቢሆን ባለፈው ዓመት ነው በሊውስ ኤነሪኬ እየተመራ በአውሮፓ ትልቁ መድረክ ላይ ንግስናውን ያወጀው። ዛሬ ድሉን ከደገመው ሁለት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ያሸነፈ የመጀመሪያው የፈረንሳይ ክለብ ይሆናል።

በዛሬው ጨዋታ በፓሪሰን ዠርማ በኩል አችራፍ ሀኪሚ ፣ ኑኖ ሜንዴዝ እና ኡስማን ዴምቤሌ ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን ሊውስ ኤነሪኬ ተናግሯል። ሞሮካዊው የቀኝ መስመር ተከላካይ ሀኪሚ ከጉዳቱ ቢያገግምም ጨዋታ ካደረገ አንድ ወር አልፎታል።

ለአርሰናልም ተከላካዩ ዩሪያን ቲምበር ተመልሷል። በብሽሽት ጉዳት ከሁለት ወር በላይ ከጉዳት የራቀው የቀኝ መስመር ተከላካዩ በጨዋታው የመሳተፍ ዕድል አለው። በመድፈኞቹ በኩል ጉዳት ላይ ከሚገኘው ቤን ዋይት ውጪ ስብስቡ የተሟላ ነው።

በሀንጋሪ ቡዳፔስት ፑሽካሽ አሬና የሚደረገው ተጠባቂ የፍፃሜ ጨዋታ ምሽት 1:00 ላይ ይጀምራል። ጨዋታውን ጀርመናዊው ዋና ዳኛ ዳንኤል ሲበርት ይመሩታል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review