AMN ግንቦት 22/2018

ያለ አስተማማኝ አህጉራዊና ቀጣናዊ ሰላም ልማትና ዕድገትን ማረጋገጥ እንደማይቻል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሞዛምቢክ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በጄኔራል ጁሊዮ ዶ ስሳንቶስ ጃኔ ከተመራ ልዑክ ጋር ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ ካሁን ቀደም የተፈራረሙትን የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ስምምነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማድረስ ያለመ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ባደረጉት ውይይት ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
በሀገራቱ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነትም በ”ፓን-አፍሪካኒዝም” መርሆዎች፣ አንድነት እና ጽናት፣ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩን የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መጠናከር የቀጣናውን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ያለ ሠላምና ፀጥታ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግናን ማሳካት እንደማይቻል ገልጸው ሽብርተኝነትን በጋራ በመዋጋት፣ በሳይበር ደኅንነትና መሠል የትብብር መስኮች ዙሪያ በቅንጅት በመስራት አህጉራዊና ቀጣናዊ ሠላምን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የሞዛምቢክ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ጁሊዮ ዶ ስሳንቶስ ጃኔ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት በልዩ ልዩ የወታደራዊ ትብብር መስኮች ዙርያ በጋራ መስራታቸው ለአህጉራዊና ቀጣናዊ ሰላም መረጋገጥ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጄኔራል ጁሊዮ ዶ ሳንቶስ ጃኔ አክለውም ከአትዮጵያ ጋር በዘርፈ ብዙ ወታራዊ የትብብር መስኮች ዙሪያ በቅንጅት መስራታችን በትምህርት እና ስልጠና ሰፊ ልምድ እና ተሞክሮ ለማግኘት ያስችልናል ብለዋል፡፡

የመከላከያ ውጪ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ የተካሄደው የሁለትዮሽ መድረክ ሀገራቱ ከአሁን ቀደም የተፈራረሙትን ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ወደ ተግባር የቀየረና ቀጣይ በሚሰሩ የትብብር ማዕቀፎች ዙሪያ አቅጣጫ ያስቀመጠ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ልማት መረጋገጥ ካላት ቁርጠኝነት የተነሳ ሞዛንቢክን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙም መግለጻቸውን ኢዜአ ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።