AMN – ግንቦት 25/2018 ዓ.ም
ገና የማለዳው ጎህ ሳይቀድና የንጋቱ ቁር በወጉ ሳይለቅ ነበር የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከሁሉ ነገር አስቀድመው፣ የነገ ሀገርን ዕጣ ፈንታ በፅኑ መሠረት ላይ ለማቆም ወደየምርጫ ጣቢያዎቹ መተምመም የጀመሩት።
ማለዳ 12፡00 ሰዓት ላይ በይፋ ለሚጀምረው ድምፅ የመስጠት ሂደት፣ ሕዝቡ ከሰዓታት በፊት ነበር ረዣዥም ሰልፎችን መያዝ የጀመረው። ይህ ተራ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት አልነበረም፤ ይልቁንም የአንድ ሕዝብ የፅናት፣ የዲሞክራሲ ፍላጎት እና የሉዓላዊነት ማሳያ ደማቅ ገጽታ እንጂ።
ንጋቱ ተገፍቶ ቀኑ ንጉሥነቱን ሲያውጅ ግን ሌላ የተፈጥሮ ፈተና መጣ። የአዲስ አበባ የቀትር ፀሐይ አናትን በሚያቀልጥ ሙቀቷ ብቅ አለች። ሆኖም የሌሊቱን ብርድ በፅናት የተቋቋመው ያ ረጅም ሰልፍ በፀሐይ ግለት ሊበተን አልቻለም።
እናቶች ጨቅላ ሕፃናቶቻቸውን አቅፈው፣ አረጋውያን በምርኩዝ ተደግፈው፣ በጤና እክል ላይ ያሉ ዜጎች ሕመማቸውን ታግለው በሰልፉ ውስጥ ብርታትን አሳይተዋል። እያንዳንዱ መራጭ የሌሊቱን ውርጭ፣ የቀኑን ሐሩር እና የምሽቱን ብርድ በትዕግሥት የተቋቋመው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለነገዋ ሀገር መሆኑን በሚገባ የተረዳ ይመስል ነበር።

በዚህ ረጅም የሰልፍ ጉዞ ውስጥ የሚስተዋለው የአንድነትና የመደጋገፍ መንፈስ ሌላኛው ውበት ነበር።
ሰልፈኛው ሰዓታትን አብሮ ሲያሳልፍ አዳዲስ ወዳጅነቶችን መስርቷል፤ አንዱ ሌላውን በጥላው ሲያስጠልል፣ ውሃና ቆሎ በፍቅር ሲጋራ ተስተውሏል።
ይህ ሰልፍ የፖለቲካ ልዩነቶች የቀለጡበት፣ ይልቁንም የጋራ መጻኢ ዕድልን በጋራ ለመወሰን ቃል የተገባበት ታላቅ የሕዝብ መድረክ መስሎ ነበር።
እያንዳንዱ ዜጋ በሰልፉ ላይ ያሳየው ትዕግሥት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የከፈለውን በዋጋ የማይተመን መስዋዕትነት ያሳያል።
ቀኑ እያዘገመ ሄዶ መደበኛው የምርጫ ማጠናቀቂያ ሰዓት፣ ማለትም ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ ደረሰ።
ነገር ግን በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ሰልፉ አሁንም ገና እልፍ አላለም ነበር። ይህንኑ ሁኔታ እና የዜጎችን ፅናትና ፍላጎት የተመለከተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ አንድም መራጭ ሳይንገላታና መብቱ ሳይሸራረፍ ድምፁን መስጠት እንዲችል በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የምርጫ ሰዓቱን እስከ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ እንዲራዘም ወሰነ።

ይህ ውሳኔ በሰልፍ ላይ ለነበሩት በሺዎች ለሚቆጠሩ መራጮች ታላቅ እፎይታን የሰጠ ሲሆን፣ የነዋሪውንም ታሪካዊ ቁርጠኝነት ወደ ላቀ ምዕራፍ አሸጋግሯል።
ዳግመኛ በመጣው የሌሊት ውርጭና ቅዝቃዜ ቢፈተንም፣ ረዣዥም ሰልፎችን ቆሞ የጠበቀው መራጭ ከግቡ ሳይደርስ እንደማይመለስ ከፊቱ ላይ በግልጽ ይነበብ ነበር።
በሞባይል መብራቶችና በምርጫ ጣቢያው ደብዛዛ ብርሃን ስር፣ እስከ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ በፅናት የቆሙት ነዋሪዎች የከተማዋን የምሽት ድባብ በታሪካዊ ተስፋ ሞልተውት አድረዋል። ነዋሪዎቹ የጣታቸውን የቀለም ምልክት እንደ ትልቅ የክብር ኒሻን በኩራት እያሳዩ በዚያ እኩለ ሌሊት ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ድምፃቸው የነገዋን ኢትዮጵያ መሠረት የሚጥል መሆኑን በኩራት እና በተግባር አረጋግጠዋል።
ይህ ታሪካዊ ዕለት፣ ተራ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያ በማናቸውም የፈተና ማዕበላት ውስጥ አልፋ የመፅናትና የመቻል አቅሟን በተግባር ያሳየችበት፣ የመዲናዋም ነዋሪዎች ፍጹም አይበገሬነት በደማቅ ቀለም የተከተበበት የታሪከ እጥፋት ጭምር ነው። እያንዳንዱ ዜጋ በሰልፉ ላይ ያሳየው ያ የማይናወጥ አቋም፣ ሀገርን በፅኑ መሠረት ላይ የማፅናት ታላቅ ወኔ መገለጫ ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ ሕዝባዊ ቁርጠኝነት፣ በሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ተንኮል ለሚያሴሩ፣ ውድቀቷንና መፈራረሷን ለሚመኙ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ባዳዎች ክፉ ሐሳብና መርዛማ ምኞት የተሰጠ ብርቱና የማያሻማ ምላሽ ነበር።
ሕዝቡ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ በፈጠረው የፅናት ማዕበል፣ የጥፋት ኃይላትን አጀንዳ ሙሉ በሙሉ በማክሸፍ የኢትዮጵያን ዘላለማዊነት በምርጫው በተግባር አስመስክሯል።
በመጨረሻም ያ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ድረስ የተዘለቀው ረጅምና አድካሚ ቀን በድል ተጠናቀቀ።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የቀኑን ፀሐይና የሌሊቱን ውርጭ በፅናት አሸንፈው፣ የተሰጣቸውን ተጨማሪ ሰዓት ተጠቅመው ያከናወኑት ይህ ተግባር በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም የሚጻፍ ገድል ነው።

ይህ ከሌሊት እስከ ሌሊት የተደረገ የፅናት ጉዞ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ለነገው ብሩህ ተስፋ የከፈለውን ክብር ሁልጊዜም ሲዘከር የሚኖር ደማቅ ታሪክ ሆኖ አልፏል።
ከንጋት እስከ ሌሊት!!
አዲስ አበባ መርጣለች!
ኢትዮጵያ መርጣለች!
በሹመት ደመቀ