AMN – ግንቦት 27/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ባጠናቀቅንበት ማግስት ዛሬ 8ኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል፡፡
ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት ዛሬ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ባለ 7 ወለል ህንፃ ገንብተን በቴክኖሎጂ ተደራጅቶ 96 ተገልጋዮችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዱ መስኮቶች ያሉት፣ በ22 ተቋማትና በ114 አገልግሎቶች ስራ አስጀምረናል ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ማዕከሉ ከፍ ባለ ጥራት እጅግ ውብ፣ ፅዱ፣ አካታች የሆነ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ፣ የህፃናት ማቆያ ያለው፣ ለሰራተኞችም ለተገልጋዮችም ምቹ ሆኖ የተገነባ ነው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም በቀጣይም በርካታ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ ማዕከል በማስገባት ነዋሪዎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እናደርጋለን ብለዋል።

የከተማችን ነዋሪዋች መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አግልግሎት ለዘመናት አስልቺ ከነበረውና ውጣ ውረድ ከበዛበት እና በእጅ መንሻ ከተማረራችሁበት ቢሮክራሲ የሚያላቅቃችሁ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ! ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በማዕከላቱ በቦታ ሳትገደቡ በሚቀርባችሁ በየትኛውም ማዕከል በመገኘት ተገልገሉ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ይህ ማዕከል ተጠናቆ ስራ እንዲጀምር ያስተባበራችሁትን በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ ብዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።