AMN — ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት 5 ዓመታት በሁሉም የቤት ልማት አማራጮች ከ496 ሺህ በላይ ቤቶችን ገንብቶ ማጠናቀቁን የከተማዋ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ አስታወቁ።
ቢሮው የቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማቀራረብ የመንግስትና የግል አጋርነትን (PPP) ጨምሮ 5 አዳዲስ አሰራሮችን በመቅረጽ ስኬታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጿል።

የቢሮ ኃላፊዋ ለኤኤምኤን እንደተናገሩት ፤ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከተያዘው እቅድ በላይ ከ179 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቤቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 50 ሺህ 305 የሚሆኑት ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶአቸው በመንግስት በጀት እየተገነቡ ያሉ መሆናቸውን ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ያደረጉትንና በቀጣይ 5 ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የታቀደውን ግዙፍ ፕሮጀክት በማንሳትም፤ የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው አዲስ አበባ ከተማ የራሷን እቅድ በእጥፍ አሳድጋ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቷን ገልጸዋል።
ለ2019 በጀት ዓመት ግንባታ የሚሆኑ መሬቶችን የማዘጋጀት፣ የኮንትራክተሮችና አማካሪዎችን የመለየት እንዲሁም የሰው ኃይል ሪፎርም ስራዎች ቀድመው መጠናቀቃቸውንም አረጋግጠዋል።
በጥራት ላይ ድርድር ሳይደረግ ወጪንና ጊዜን የሚቆጥቡ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችም በስፋት ጥቅም ላይ መዋል መጀመራቸውን ኃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ ባለፉት 5 ዓመታት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በሚወጡ ባለሀብቶችና በበጎ አድራጊዎች አማካኝነት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ከ46 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተው መተላለፋቸዉንም አስታውቀዋል።
ይህ ሰው ተኮር የበጎ አድራጎት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በተለይም አሁን ባለው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅትም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የቤት እድሳትና ግንባታዎች በየክፍለ ከተማው በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በወርቅነህ አቢዮ