AMN ግንቦት 29/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ ቆጠራ ሂደት አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ እንደገለፁት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄዳባቸው በ825 የምርጫ ክልሎች የድምፅ ቆጠራ ውጤት በምርጫ ክልል ደረጃ ይፋ መደረጋቸዉን እና ቀሪዎቹ ምርጫ ክልሎች የማዳመር ስራቸውን መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የምርጫ ክልሎች መካከል 11ዱ የምርጫ ክልሎች የቆጠራ ውጤታቸውን በምርጫ ክልል ደረጃ መለጠፋቸውንም ሰብሳቢዋ ገልፀዋል።
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ 47 ያህል ቅሬታዎች የቀረቡለት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 31 ቅሬታዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ 16 ቅሬታዎች ደግሞ ከግል እጩዎች የቀረቡ መሆናቸውን ወ/ሮ ሜላትወርቅ አብራርተዋል። ቦርዱ ቅሬታዎችን በህግና አሰራሩ መሰረት እየመረመረና ምላሽ እየሰጠባቸው እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በታዛቢነት የተሳተፉ በርካታ ሲቪል ድርጅቶችና ሌሎች አካላትም ሪፖርቶቻቸውን ለቦርዱ ማቅረባቸውን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

በቀሪ ጊዜያት ድምፅ የማዳመር ስራዎችን በሁሉም ምርጫ ክልሎች ማጠናቀቅ፣ ወደ ማዕከል ማጓጓዝና የመጨረሻ ውጤት ሂደትን ማጠናቀር ቦርዱ እንደሚሰራ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ገልፀዋል።
በይታያል አጥናፉ