AMN- ግንቦት 30/2018 ዓ.ም
ፎሎረንቲኖ ፔሬዝ የሪያል ማድሪድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እየመሩ እንደሚገኙ ማርካ ዘገቧል። አሁንም ክለቡን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ፔሬዝ ከኤነሪኬ ሪኬልሜ ጋር እየተፎካከሩ ይገኛሉ።
የ79 ዓመቱ አዛውንት የስልጣን ጊዜያቸው ሳያበቃ ነው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲደረግ ውሳኔ ያሳለፉት። ምክንያታቸው ደግሞ ሪያል ማድሪድ ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመት ያለ ዋንጫ ማጠናቀቁ ተቃዋሚ በዝቶባቸዋል የሚለውን አሉባልታ ማጥፋት ነው።
አሁንም የደጋፊዎች ተመራጩ ፕሬዝዳንት እኔ ነኝ የሚለውን ለማስመስከር ያመቻቹት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም እየመሩ ይገኛሉ። የሪያል ማድሪድ ልሳን እንደሆነ ሚነገርለት ማርካ እንደዘገበው እስካሁን ባለው ሂደት ፔሬዝ 334 ድምፅ ሲያገኙ ተፎካካሪያቸው ኤነሪኬ ሪኬልሜ 168 ድምፅ አግኝተዋል። ምርጫውም እስከ ምሽቱ 3፡00 ይቀጥላል።
ፎሎረንቲኖ ፔሬዝ ከ2000 – 2006 ለመጀመሪያ ጊዜ ማድሪድን ከመሩ በኋላ በ2009 ተመልሰዋል። እስካሁንም መንበረ ስልጣኑ በእጃቸው ይገኛል።
የዛሬውን ምርጫ ካሸነፉ ጆዜ ሞሪንሆ ዳግም ወደ ሪያል ማድሪድ ይመለሳሉ ፤ ኢብራሂማ ኮናቴ እና ዴንዝል ዱምፍሪስ ነጩን መለያ እንደሚለብሱ ይፋ ይሆናል። ለአንድ ወጣት ተጫዋች 150 ሚሊየን ዩሮ መድቤያለሁ ያሉት ኮከብም ማን እንደሆነ ይለያል ተብሎ ይጠበቃል።
በሸዋንግዛው ግርማ