AMN-ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

ከዓለማችን ታላላቅ ማራቶኖች አንዱ የሆነው የበርሊን ማራቶን፣ በመጪው መስከረም ወር አጋማሽ በጀርመን መዲና ይካሄዳል። በዚህ በጉጉት በሚጠበቀው ውድድር ላይ ከሚሳተፉ ታዋቂ አትሌቶች መካከል ትዕግስት አሰፋ አንዷ መሆኗ ታውቋል።

የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ትዕግስት፤ የማራቶን የዓለም ሪከርድን ለመስበር እንደምትሮጥ ይጠበቃል። አትሌቷ በኬንያዊቷ ሩት ቼፕጌቲች የተያዘውን 2 ሰዓት ከ09 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ የዓለም ሪከርድ ታሻሽላለች ተብሎ ከፍተኛ ግምት አግኝታለች። የፈረንጆቹ 2022ቱ እና 2023ቱ የበርሊን ማራቶን አሸናፊዋ ትዕግስት፣ የለንደን ማራቶንን ለሁለት ተከታታይ ዓመታት አሸንፋ ነው ወደ በርሊን የምትጓዘው።

‹‹ከሶስት ዓመታት በፊት የዓለም ሪከርድ በሰበርኩባት በርሊን ለሶስተኛ ጊዜ የመወዳደር እድል በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ሰዓት ለማስመዝገብ እሮጣለሁ›› ማለቷን የጀርመን መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል። እዚያው በርሊን ላይ 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመግባት በሴቶች ብቻ ማራቶን የዓለም ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነችው ትዕግስት፣ ዘንድሮ በበርሊን የድል ‘ሃትሪክ’ ለመስራት ከወዲሁ ቅድሚያ ግምቱን አግኝታለች።

በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና የማራቶን አሸናፊዋ አማኔ በሪሶም በዘንድሮው የበርሊን ማራቶን ከሚጠበቁ ጠንካራ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። ከበርካታ ዓመታት ጉዳት በኋላ ወደ ውድድር የተመለሰችው አማኔ፣ በርሊን ላይ ድል ለመቀዳጀት ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ተፎካካሪዎች ተርታ ተሰልፋለች።

በሌላ በኩል የባለፈው ዓመት አሸናፊዋ ኬንያዊት ሮዝሜሪ ዋንጂሩም ቀላል ግምት አልተሰጣትም። በ2022ቱ የበርሊን ማራቶን ትዕግስት አሰፋን ተከትላ በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው ዋንጂሩ፣ የ2025ቱ የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል።
በታምራት አበራ