ስኬት ባንክና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ደንበኞች የፋይናንስ አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

You are currently viewing ስኬት ባንክና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ደንበኞች የፋይናንስ አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

AMN- ሰኔ 4/2018 ዓ.ም

ስኬት ባንክ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመጋዘን ደረሰኝ ፋይናንስን በማጠናከር ለገበያ ተሳታፊዎች የብድር ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የስኬት ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ዳምጠው አለማየሁ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መርጊያ ባይሳ ናቸው፡፡

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ዳምጠው አለማየሁ፤ ባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ፤ የካርድ ባንኪንግና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ዲጂታል የፋይናንስ ብድር አገልግሎትና ስኬት አልነጃህ የተሰኘ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይሄም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚሰጡ የመጋዘን ደረሰኞችን ለብድር ዋስትና አድርጎ በመቀበል ለገበያ አባላትና ደንበኞች የፋይናንስ አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

የተደረሰው የአጋርነት ስምምነትም በምርትና በንግድ ላይ ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ትልቅ እፎይታን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መርጊያ ባይሳ በበኩላቸው፤ ምርት ገበያው አብረውት የሚሰሩ ባንኮች ቁጥር 27 መድረሱን ጠቁመው ባለፉት 18 ዓመታት በምርት ገበያው በኩል 430 ቢሊዮን ብር ገደማ ማገበያየቱን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት 10 ወራት ብቻ ላኪዎችና ነጋዴዎች ከ96 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት በዲጂታል አማካኝነት መገበያየት መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለዘመናዊ የኦንላይን ግብይት ስርዓትና ለጤናማ የገንዘብ ዝውውር መሳለጥ ከስኬት ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የተደረሰው ስምምነት እንደ ትልቅ ስኬት የሚወሰድ መሆኑንም ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የገለፁት፡፡

ባንኩ ጠቅላላ ሃብቱ 24 ቢሊየን ብር፤ ጠቅላላ ካፒታሉን ደግሞ 10 ቢሊየን ብር በማድረስ የደንበኞቹን ቁጥር 795 ሺህ ማድረሱ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review