AMN- ሰኔ 5/2018 ዓ.ም
23ኛው የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ የጣምራ አዘጋጆቹ አሜሪካ እና ካናዳ የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ የምታስተናግደው ካናዳ ከቦስኒያ ሄርዞጎቪና ጋር ትጫወታለች። በቶሮንቶ ስታዲየም የሚከናወነው ጨዋታ ለካናዳ ሰባተኛ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዋ ይሆናል።
በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ጄሴ ማርሽ የሚመሩት ካናዳዎች ከዚህ ቀደም ሁለት የዓለም ዋንጫ ተሳትፎአቸው ስድስት ጨዋታ አድርገው ምንም ነጠብ አላስመዘገቡም። በሸንፈት በደመደሟቸው በእነዚህ ጨዋታዎች ሁለት ግብ ብቻ አስቆጥረው 12 ደግሞ ተቆጥሮባቸዋል።
ካናዳ ይህን መጥፎ ታሪካቸውን ለመቀየር ጥሩ ቁመና ላይ ናቸው።

ብሔራዊ ቡድኑ 2026 ከገባ አንድም ጨዋታ አልተሸነፈም። በተለይ የተከላካይ ክፍላቸው ጠንካራ ነው። በመጨረሻ ስምንት ጨዋታዎች በስድስቱ የግብ መረባቸውን ሳያስነኩ ወጥተዋል።
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ጣልያንን ጥላ ያለፈችው ቦስኒያ ሄርዞጎቪና ቀላል ተጋጣሚ አይደለችም። አውሮፓዊቷ ሀገር ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ትሳተፋለች።
በምድብ ሁለት የተደለደሉት ካናዳ እና ቦስኒያ በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በቶሮንቶ ስታዲየም የሚከናወነው ጨዋታ ምሽት 4፡00 ይጀምራል።
ዘንድሮ ከሚከናወኑ 104 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች 78ቱን የምታስተናግደው አሜሪካ ከፓራጓይ የምታደርገው ፍልሚያ የዛሬ መርሃግብር አካል ነው። የእግርኳስ ትልቁን መድረክ ለሁለተኛ ጊዜ የምታሰናዳው አሜሪካ ትልቁ ውጤቷ 1930 የዓለም ዋንጫ ላይ የነሐስ ሜዳልያ ያገኘችበት እንደሆነ ታሪኳ ያሳያል።

ሀገሪቱ ከዚህ ውጪ በ2002 ሩብ ፍፃሜ የደረሰችበት ትልቁ ስኬት ተደርጎ ይቆጠርላታል። በማውሪሲዮ ፖቼቲንሆ ስር ሁለት ዓመት የሆነው ብሔራዊ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው ውጤት የተሻለ ያስመዘግባል ተብሎ አይጠበቅም።
የደቡብ አሜሪካ ተወካይዋ ፓራጓይ ዘንድሮ ዘጠነኛ ተሳትፎዋን ታደርጋለች። ሀገሪቱ ሩብ ፍፃሜ ደርሳ ካጠናቀቀችበት 2010 በኋላ ወደ ታላቁ መድረክ ስትመለስ የመጀመሪያዋ ነው።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ለሁለተኛ ጊዜ ይገናኛሉ፤ ከዚህ ቀደም በ1930 ባደረጉት ጨዋታ አሜሪካ 3ለ0 አሸንፋ ነበር። የዛሬ ጨዋታ ለሊት 10፡00 ከ70 ሺህ በላይ ተመልካች በሚይዘው ሶፊ ስታዲየም ይከናወናል።
በሸዋንግዛው ግርማ