AMN- ሰኔ 06/2018 ዓ.ም

አፍሪካዊያን በአህጉሪቱ የሚከሰቱ በሽታዎችን በቅንጅ መከላከል እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ሰሀረላ አብዱላሂ ገለጹ፡፡
የደቡብ ሱዳንና የሶማሌ ላንድ የጤና ባለሙያዎች በአዲስ አባባ የተከናወኑ የጤና መሰረተ ልማቶችን እየጎበኙ ነው።

እንደ ሀገር በጤናው ዘርፍ በተከናወነው የሪፎርም ስራ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ያሉት የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ሰሀረላ አብዱላሂ፣ በዘርፉ ከአጎራባች ሀገራት ጋር ያላትን ቅንጅት ለማጠናከርም የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች ነው ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ 400 ለሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ስኮላር እየሰጠች ትገኛለች ብለዋል።

በዛሬው እለትም በተለያዩ የትምህር ተቋማት ሲማሩ የቆዩ የደቡብ ሱዳንና የሶማሌ ላንድ የጤና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ የተለያዩ የጤና መሰረተ ልማቶችን እንዲጎበኙ ተደርጓል ነው ያሉት።
ይህም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተሞክሮ ለሀገራቱ ከማጋራት ባሻግር በአፍሪካ የሚከሰቱ በሽታዎችን በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም አንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጎረቤትን የሚያስቀድም ዲፕሎማሲን ትከተላለች ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ የሀገራቱ ጤና ባለሙያዎች የሚያደርጉት ጉብኝትም በሀገራቱ መካከል ያለውን የጤና ዘርፍ ትስስርን ከማጎልበት ባሻገር የሀገራቱን ሁሉን አቀፍ ዲብሎማሲያዊ ግንኙነትን በማጎልበት በኩል የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም መሪነቷን የሚያጠናክርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጎልበት የባህል ዲፕሎማሲን የሚየጎለብት መሆኑንም ገልጸዋል።