AMN- ሰኔ 21/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ የፖለቲካ ውጣ ውረዶችን፣ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን አስተናግዳለች።
ለዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ልዩነቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አስተማማኙ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በሀሳብ መሞገትና በምክክር መግባባት መሆኑ ጥርጥር የለውም።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8 ጀምሮ ለሚካሄደው ታሪካዊ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 8 ዋና ዋና አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ኮሚሽኑ በዝርዝር ይፋ ያደረጋቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች የሀገር ግንባታ ፣ የመንግስት አደረጃጀት ቅርፅ እንዲሁም የምርጫ ስርዓት ፣ የፌዴራል ከተሞች ጉዳይ (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች ፣ የተቋማት ግንባታ የህግ የበላይነት እና ሰበአዊ መብቶች ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ እና አርብቶአደሮች ጉዳዮች ፣ ሙስና እና መልካም አስተዳደር እና ሰላም ግንባታ ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ ይፋ ያደረጋቸው አጀንዳዎች የኢትዮጵያን ነባራዊ ችግሮች ከስራቸው መፈተሽ የሚያስችሉና የጋራ መግባባት ሊደረስባቸው የሚገቡ መሰረታዊ፣ ተገቢና ወቅታዊነት ያላቸው ናቸው፡፡
እንደ የሀገር ግንባታ እና የመንግስት አደረጃጀት ያሉ አጀንዳዎች መካተታቸው የትኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የማያገል የጋራ ሀገራዊ ማንነት ለመቅረጽ የሚያስችል አውድ የሚፈጥር ነው።
የተቋማት ግንባታ ፣ የህግ የበላይነት እና ሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች በአጀንዳነት መቅረጽ ፍትሃዊ ስርዓት ለመዘርጋት መሰረት ይጥላል።
የአርሶ አደሩ እና የአርብቶ አደሩ አንገብጋቢ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች እንዲሁም ዘላቂ የሰላም ግንባታ ጉዳዮች መካተታቸው፣ ምክክሩ የፖለቲካ ልሂቃን ብቻ ሳይሆን የሰፊው ህዝብ የኑሮ እና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያረጋግጣል።
ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠረው ሁሉም ወገን እኩል የሚደመጥበት እና የጋራ መፍትሄ የሚፈለግበት መድረክ ሲኖር እንደመሆኑ ከሐምሌ 8 ጀምሮ የሚካሄደው ጉባኤ ልዩነቶች በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሀሳብ ብልጫ የሚፈቱበት ፣ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የማይሆንበት ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መድረክ ይሆናል፡፡
ባለፉት የኢትዮጵያ ታሪኮች የተደረጉ የመንግስት ለውጦች ሁሉ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ያልቻሉት፣ መሰረታዊ የሀገር ግንባታ ጥያቄዎችን በምክክር መፍታት ባለመቻላቸው እንደሆነ የፖለቲካ ልሂቃን ይጠቅሳሉ።
ይህ የምክክር ጉባኤ የማይናወጥ ህገ-መንግስታዊ እና ተቋማዊ መሰረት በመጣል ዜጎች በሀገራቸው ላይ እምነት እንዲያሳድሩ የሚያደርግ ይሆናል።
ሐምሌ 8 የሚጀምረው ጉባኤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶችና የመላው ህዝብ ተወካዮች በሀቀኝነት፣ በቀና ልብ እና ለሀገር በሚበጅ አስተዋይነት የሚሳተፉበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
አጀንዳዎቹ በአግባቡ ተፈትሸው የጋራ መግባባት ከተደረሰባቸው በፅኑ መሰረት ላይ የቆመች እና የሰላም ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገው ጉዞ እውን ይሆናል።
በታደሠ ሽፈራው