AMN ሰኔ 7/2018

የቀድሞ ሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሥት በመፈፀም ያለግጭትና ብጥብጥ እንደማይኖር በተግባር ያሳየ መሆኑን የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ገለጹ።
የተለያዩ አገራት መንግሥታት፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትና የልማት አጋሮች የትግራይ ክልልን የሰላም ሂደት በሚያደናቅፈው የሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን ላይ ግልጽና ጠንካራ አቋም እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት፤ የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለማስጠበቅ ያሳየው ከፍተኛ ትዕግስት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የቀድሞ ሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን የፌዴራል መንግሥት በመልሶ ግንባታና በፖለቲካ አስተዳደር የሰላም ስምምነቱን ለማስከበር ያደረገውን ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደናቅፍ መቆየቱን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅትም የትግራይ ክልል ህዝብ የዳግም ጦርነት ሙከራን አጥብቆ እየተቃወመ እንደሚገኝ አመልክተው፤ የቀድሞ ሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን ክልሉን ወደ ዳግም ጦርነት ለማስገባት እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሥት በመፈፀም ያለግጭት እንደማይኖር ሕገ-ወጥነቱን በተግባር እንዳሳየ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሕገ-ወጡ የቀድሞ ሕወሓት ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ በማካሄድ በወጣቶች ላይ የከፋ እንግልት እየፈጸመ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የትግራይ ክልል ያልተፈቱ የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዮችም በውይይት፣ ሕገ-መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ በወታደራዊ አካሄድ እንደማይፈቱ አስገንዝበዋል።
የትግራይ ክልል ከዓመታት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ከደረሰበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉስቁልና ሳያገግም ሌላ ግጭት መሸከም እንደማይችል ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ባንዳና የውጭ ባዕዳን ጸረ-ሰላም ኃይሎችም የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋት ”ጽምዶ” በሚል ጥምረት የክህደት እንቅስቃሴ እያዳረጉ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይህ የጥፋት እንቅስቃሴም ቀጣናዊ የሰላም መናጋትን የሚያስከትል በመሆኑ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር ሊወገዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ለዚህም መንግሥታት፣ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሰላም ሂደት ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ማውገዝና ጠንካራ አቋም መውሰድ አለባቸው ብለዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በትግራይ ክልል የደረሰውን ጉዳት ማገገም የሚያስችል በመልሶ ግንባታ፣ ልማትና በዕርቅ ላይ የተመሰረተ ምኅዳር እንዲፈጠር ያደረገ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም አቀፍ ማህበረሰብም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ለትግራይ ክልል ህዝብ ያስገኘውን እፎይታ ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶችን በጥብቅ በማውገዝ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ በሰላም ላይ የተመሰረተ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ክንደያ፤ ባለፈው ግጭት የተፈጠረው ጉዳትም በመልሶ ግንባታ፣ልማትና ብሔራዊ ዕርቅ መፍታት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡