ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ምን ውጤት አስገኘ?

AMN – ሰኔ 07/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ክብር ማስከበርን ማዕከል ያደረገውን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መተግበር ከጀመረች ወዲህ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ዘርፎች ተጨባጭና ስር ነቀል ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን የመንግስትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፖርቶች ያሳያሉ።

ይህ ፖሊሲ ከወትሮው የተለየና እያንዳንዱን ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ቀደም ሲል የነበሩ የዲፕሎማሲ ስራዎች በይበልጥ በይፋዊና በንግድ ግንኙነቶች ላይ ብቻ ያተኮሩ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የዜጎች ክብርና ደህንነት ቀዳሚ ተግባር ሆኗል።

በዲፕሎማሲው አማካኝነት በውጭ ሀገር የሚሰሩ ዜጎችን መብት ለማስከበር ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከኳታርና ከጆርዳን መንግስታት ጋር የሁለትዮሽ የሰራተኛ ስምምነት ተፈርሟል።

ይህም ዜጎች በህጋዊ መንገድ እንዲቀጠሩ፣ ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እንዲወሰንላቸውና የህክምና ዋስትና እንዲኖራቸው አስችሏል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪነት በተካሄደ መጠነ-ሰፊ እንቅስቃሴ ፣ በሳዑዲ አረቢያ በችግርና በእስር ላይ የነበሩ ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን በክብር ወደ ሀገራቸው የመመለስና የማቋቋም ስራ ተከናውኗል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጋር በመተባበር የኢ-ቪዛ እና የኦንላይን ፓስፖርት እድሳት አሰራርን ለመዘርጋት አስችሎታል።

ይህም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በአካል ሳይንገላቱ በዲጂታል አማራጭ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል።

በመንግስትና በውጭ በሚኖሩ ዜጎች መካከል ያለው መተማመን ማደጉ የዳያስፖራውን የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል።

በዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት፣ ዳያስፖራው በህጋዊ የባንክ መስመሮች ወደ ሀገር ውስጥ የሚልከው የሃዋላ መጠን በየዓመቱ እየጨመረ ይገኛል። ይህም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እያቃለለ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የዳያስፖራ አባላት በሀገር ውስጥ የፋይናንስ ዘርፍ መክፈትን ተከትሎ በፊንቴክ ፣ በዲጂታል ባንኪንግ፣ በግል ጤና ተቋማትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ለሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ያላቸው ድጋፍ ተጠናክሯል፡፡

እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኮሪደር ልማት፣ የገበታ ለሀገር እና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ላይ ዳያስፖራው በገንዘብ፣ በእውቀትና በቁሳቁስ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ኢትዮጵያ ታሪካዊና ወቅታዊ ፈተናዎች በገጠሟት ወቅት በውጭ የሚኖሩ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ አደባባዮች ሰልፎችን በማደራጀትና በማህበራዊ ሚዲያ ንቁ ዘመቻ በማድረግ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት አስከብረዋል።

መንግስት ባቀረበው ጥሪ መሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች በአንድ ጊዜ ወደ ሀገር ቤት በመግባት የሀገሪቱን ሰላምና የቱሪስት መዳረሻዎች ለዓለም ማህበረሰብ በተግባር አስተዋውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት እንደ አዲስ መዋቀሩ ስራውን ተቋማዊና ዘላቂ አድርጎታል።

በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚመራው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ መቋቋሙ፣ ዳያስፖራው በቀጥታ ለማህበራዊ ፕሮጀክቶች ማለትም ለትምህርት ቤቶች፣ ለጤና ተቋማትና ለንጹህ መጠጥ ውሃ የሚያደርገውን ድጋፍ ስኬታማ አድርጎታል።

ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥንካሬን፣ የኢኮኖሚ መረጋጋትን እና የዜጎችን ክብር ያስገኘ ስትራቴጂ በመሆኑ በቀጣይም ይህንን ግንኙነት በዲጂታል መሠረተ ልማቶች በታገዘ ሁኔታ ይበልጥ ማጠናከር የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት እንደሚያፋጥን የዘርፉ ምሁራን ያስገነዝባሉ።

በአስማረ መኮንን

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review