ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ ስትዘጋጅ የችግኝ ተከላ ግቧን ወደ 65 ቢሊየን አሳደገች

You are currently viewing ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ ስትዘጋጅ የችግኝ ተከላ ግቧን ወደ 65 ቢሊየን አሳደገች

AMN – ሰኔ 9/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2027 ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ32) እንደ አንድ ትልቅ የዝግጅት አካል በመጠቀም ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሯን በማጠናከር አጠቃላይ የተተከሉ ችግኞችን ቁጥር 65 ቢሊዮን ለማድረስ ማቀዷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያመለከቱት በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ሀገሪቱ እስካሁን ባደረገችው የተቀናጀ የሕዝብ ንቅናቄ 48 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል የቻለች ሲሆን፣ ይህ ስኬትም ዓለም አቀፍ ትኩረትን በመሳብ የኮፕ32 ጉባኤን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ለመጀመሪያ ጊዜ እንድታስተናግድ ዕድል እንደፈጠረላት ጠቁመዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በቀጣዩ 2027 መጨረሻ ላይ በሚካሄደው በዚህ ታላቅ ጉባኤ ፣ ከ70 ሺህ እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ የዓለም እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ጉባኤ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል፣ ዓለም ያልቻለውን የችግኝ ተከላ ሥራ ኢትዮጵያ በተግባር በማሳየቷ መሆኑ ተገልጿል።

በያዝነው የክረምት ወቅት ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በዚህም አጠቃላይ የተተከሉ ችግኞች ቁጥር ወደ 56 ቢሊዮን ከፍ እንደሚል አስረድተዋል።

ይህን አሀዝ 65 ቢሊየን የማድረስ ግብ መያዙን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገለጹት፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግኝ መትከልን የዕለት ተዕለት ሥራቸው አካል እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review