የምርጫ ቦርድ ከየትኛውም አካል ነፃ ሆኖ ሥራውን በአግባቡ አከናውኗል- ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ

AMN- ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

የምርጫ ቦርድ ከየትኛውም አካል ነፃ ሆኖ ሥራውን በአግባቡ ማከናወኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተናገሩ።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በመርሐ ግብሩ የቦርዱን የምርጫ አፈፃፀም ያቀረቡት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ ቦርዱ ምርጫው ስኬታማ፣ ፍትሀዊና ሁሉንም ያካተተ እንዲሆን በትኩረት ሰርቷል ብለዋል።

በምርጫ ወቅት የሴቶች ሁለንተናዊ ጥቃት በመከላከል፣ ምርጫው ዘመናዊነትን እንዲላበስ ከምዝገባ ጀምሮ በዲጂታል መንገድ እንዲከናወን የተደረገበት መንገድ ታሪካዊ የምርጫ ዘመናዊነት ጅማሮ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ5 ሚሊየን በላይ ዜጎች በኦንላይን መንገድ ተመዝግበዋል ሲሉ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ገልፀዋል።

ወ/ሮ ሜላትወርቅ አክለውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የምርጫ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ርዕዮተ ዓለማቸውን ለህዝብ ለማድረስ እንዲችሉ የምርጫ ክርክር መድረክ ከማድረግ ጀምሮ ስልጠና እንዲያገኙ የተደረገበት መንገድ ለተሻለ ተቋምና ሀገራዊ ግንባታ ወሳኝ ተግባር ነበር ብለዋል።

የምርጫ ቁሳቁሶች በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ፍትሀዊና ግልፅ በሆነ መንገድ ተጓጉዘው በጊዜ እንዲደርሱ ስለመደረጉም ወ/ሮ ሜላትወርቅ ተናግረዋል።

የምርጫውን ሂደት ለማህበረሰቡ በማቅረብ የምርጫውን ፍትሀዊነት ያረጋገጡ የሚዲያ አካላት ሚናቸው የጎላ እንደነበርም አንስተዋል።

የምርጫውን ፍትሀዊነት ከሚያረጋግጡ ጉዳዮች መካከል የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ታዛቢዎች ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review