በአዲስ አበባ ለምርጫ ከተመዘገቡ ዜጎች 96 በመቶው ድምፅ ሰጥተዋል፤ የህዝቡ የሰላምና የልማት ፍላጎት በተግባር ተገልጿል

AMN- ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በድል ተወጥተዋል ኢትዮጵያም ለተቀረው ዓለም ምሳሌ በመሆን አሸንፋለች።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመራጭነት ከተመዘገቡት ከ1.9 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች መካከል 96 በመቶው በምርጫው ዕለት በነቂስ በመውጣት ድምፅ መስጠታቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህዝብ ተሳትፎ ሀገሪቱ ለጀመረችው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ የከፈተና የህዝቡን የሰላም፣ የፍትህ እንዲሁም የልማት ፍላጎት በግልጽ ያሳየ መሆኑንም ያመላክታል።

በምርጫው ዕለት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ማለዳ ወፍ ሳይንጫጫ ቀድመው በየምርጫ ጣቢያዎቹ በመገኘት ረጅም ሰልፎችን መያዝ ጀምረው ነበር።

ሂደቱ እጅግ አድካሚና በብዙ ጣቢያዎች ላይ እስከ ሌሊት ድረስ በዘለቀበት ወቅትም፣ መራጩ ህዝብ ያሳየው ትዕግስትና ጨዋነት የሚደነቅ ነበር።

ዜጎች ቅዝቃዜውንና ድካሙን ተቋቁመው፣ ሌሊቱንም ጭምር አምሽተው ለመምረጥ ያሳዩት ፅናትና ሥነ-ስርዓት፣ ለዲሞክራሲያዊ መብታቸው መከበርና ለሀገራዊ መረጋጋት ያላቸውን የላቀ ባለቤትነት በተግባር ያረጋገጠ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ ታሪካዊ ትዕይንት ህዝቡ የሀገሩን እጣ ፈንታ በራሱ ድምፅ ለመወሰን ያለውን ቆራጥነት ለዓለም ያስመሰከረበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

ይህ 96 ከመቶ የደረሰው እጅግ ከፍተኛ የመራጮች ቁጥር በከተማዋ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን በግልጽ ያሳያል።

በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ወሳኝ ምሰሶ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ ከፍተኛ ቁጥር ማህበረሰቡ በምርጫ ሥነ-ስርዓትና በህጋዊ መንገድ ስልጣንን በማስተላለፍ ሂደት ላይ ያለውን እምነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ይኸው ተሳትፎ ወደፊት ለሚመሰረቱ የመንግስት አካላት እና ተቋማት ጠንካራ ህዝባዊ ቅቡልነትን የሚሰጥ በመሆኑ፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ጠንካራ የፖለቲካ ባህልን ለመገንባት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው ድምፃቸውን መስጠታቸው ፍፁም ሀገራዊ በሆነና የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ታሳቢ ባደረገ የሰላምና የልማት ፍላጎት ላይ ተመስርተው መሆኑን ፍንትው አድርጎም ይገልፃል።

ይህ ከፍተኛ ቁጥር በከተማዋም ሆነ በሀገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማትና የኢኮኖሚ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ካለው ከፍተኛ ፍላጎትና ተስፋ በመነሳት መሆኑን የምርጫው ሂደት ማሳያ ነው።

የአዲስ አበባ መራጮች አርአያነት ያለው ተሳትፎ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ጉዞ ላይ አዲስ ተስፋ የሰነቀና የዜጎችን የጋራ ራዕይ በተግባር ያሳየ ሆኖ በክብር መዝገብ ተመዝግቧል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review