AMN- ሰኔ 15/2018 ዓ.ም

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የምርጫ ቦርድ አባላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ህብረት አባሆይ፣ በምርጫው በሴቶች የሚደርስ ጥቃት ለመከላከል መረጃዎችን የመተንተን ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም ምርጫውን አንዲታዘቡና የታዘቡትን እንዲመዝግቡ ቅፅ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም አስታውሰዋል።
በዚህ መሠረት 7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በአብዛኞቹ የምርጫ አካባቢዎች ሰላማዊ፣ ሥርዓት ባለውና ግልጽ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ማኅበሩ ከታዛቢዎቹ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት፣ ከተሸፈኑት የምርጫ አካባቢዎች መካከል 97.8 በመቶ የሚሆነው ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ድባብ የተከናወነ ሲሆን፣ ይህም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለጸጥታ ኃይሎችና ለሰላማዊ መራጮች የተቀናጀ ጥረት ስኬት ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም 92.5 በመቶ የሚሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች ለነፍሰ ጡርና ለሚያጠቡ እናቶች፣ ለአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ በመስጠት ሁሉን አካታች አሠራርን ተግባራዊ ማድረጋቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

በቅድመ-ምርጫ ወቅት የኔዘርላንድስ የባለብዙ ፓርቲ ዲሞክራሲ ተቋም ባዋቀረው ኮሚቴ አማካኝነት 42 የተለያዩ የጥቃት ዓይነቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
በዕለቱም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጥሪ ማዕከል 8 አስተዳደራዊ ምላሽ የተሰጠባቸው ሪፖርቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ከቲምራን 11 ጥቆማዎች፣ ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር 6 ጥቆማዎች፣ እንዲሁም ከፖሊስ 1 ጥቆማ ቀርቦ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል ሲሉ ዝርዝሩን አቅርበዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፣ ሴቶች ያለስጋት ድምፃቸውን እንዲሰጡና ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሚካኤል ህሩይ