AMN- ሰኔ 16/2018 ዓ.ም
በመዲናዋ እጅግ ለከፋ የቤትና የማኅበራዊ ችግር ተጋላጭ የነበሩ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችን ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ እየታደገ የሚገኘው “የበጎነት መንደር” ትልቅ ተስፋ እየሆነ መጥቷል።
ቀደም ሲል በመጠለያ እጥረት፣ በከፍተኛ የኪራይ ውድነት እና ለኑሮ ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች ይኖሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችንና አቅመ ደካሞችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያስቻሉ በርካታ ብሎኮችና ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ይታወቃል።
ይህ ግዙፍ ማኅበራዊ ተግባር ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት ባለፈ፣ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የሕይወት ዋስትና ያረጋገጠ ነው።

በበጎነት መንደር የሚገነቡት የመኖሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ የጋራ የመመገቢያ አዳራሾች፣ ዘመናዊ፣ የመዝናኛና የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ እንዲሁም አረንጓዴ ሥፍራዎች ጭምር በመሆናቸው ነዋሪዎቹ ክብር ያለውና የተሟላ ሕይወት እንዲመሩ አግዟል።
ቀደም ሲል ተበታትነውና በከባድ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ የነበሩ ዜጎች አሁን ላይ በአንድ መንደር ተሰባስበው እርስ በርስ የሚደጋገፉበት ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር መፈጠሩ የፕሮጀክቱ ሌላኛው ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህንን ስኬታማ ተሞክሮ ይበልጥ ለማስፋፋት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በትላንትናው ዕለት አዲስ ግዙፍ ግንባታ በይፋ አስጀምረዋል።
ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጀርባ የሚገነባውና እጅግ የተጎሳቆሉ መኖሪያ ቤቶችን ወደ ንፁህና ውብ መንደር የሚቀይረውን የ“አራዳ የበጎነት መንደር” ግንባታን ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስጀመሩት፡፡

በትላንትናው ዕለት ግንባታው የተጀመረው አዲሱ የበጎነት መንደር ባለ 9 ወለል 8 ዘመናዊ ሕንፃዎችን፣ ሁለት ባለ 4 ወለል የገበያ ማዕከላትን እንደሚያካትትም ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአጠቃላይ 2 ሺህ 500 ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ከንቲባዋ አክለውም ይህ ግንባታ የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን በመቀየር ለኑሮ ምቹ የሆኑ፣ ንጽሕናቸውን የጠበቁ የመኖሪያ ቤቶች፣ የጋራ መገልገያዎች፣ አረንጓዴ ሥፍራዎችና ሕፃናት ቦርቀው የሚጫወቱባቸው የላቁ የስፖርት ሜዳዎችን እንደሚያካትትም ገልጸዋል፡፡
የአራዳ የበጎነት መንደር ለሰው ልጆች ምቹና ክብር የሚመጥን ዘመናዊ አኗኗርን በመፍጠር የከተማዋን ውበትና ገጽታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።
የበጎነት መንደር በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የቤት እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍና የዜጎችን ማኅበራዊ ሕይወት ለመታደግ ለሚደረገው ጥረት እንደ ትልቅ ማሳያ የሚወሰድ ስኬታማ ተግባር ነው፡፡
በአስማረ መኮንን