AMN- ሰኔ 16/2018 ዓ.ም
አሜሪካ በቀድሞ ሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን አመራሮችና በቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የጣለችው የቪዛ እገዳ ቡድኑ የሚፈጽመውን ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያቆም የተላለፈ ግልጽ መልዕክትና ከፍተኛ ውሳኔ መሆኑን የስምረት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ገብረጻዲቅ ገለጹ።
የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር እና የስምረት ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አልማዝ ገብረጻዲቅ በቅርቡ የተጣለውን የቪዛ እገዳ እና በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ኃላፊዋ እንደገለጹት፣ አሜሪካ በቀድሞው የሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን አመራሮች እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የጣለችው የቪዛ እገዳ ቡድኑ ህገወጥ የሆኑ እኩይ እንቅስቃሴዎችን በአስቸኳይ እንዲያቆም የተላለፈ ግልጽ መልዕክት ነው።
ይህ ውሳኔ ቡድኑ ቆም ብሎ እንዲያስብና የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
የቀድሞ ሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን በትግራይ ክልል ለጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለጹት የስምረት ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊዋ፤ በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ የወጣቶች አፈሳ እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በክልሉ እምቢ ያሉ ወጣቶች በህገወጥ መንገድ በተዘጋጀ አዋጅ በተደነገገ ቅጣት በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ታጣቂ ቡድኑ እንዲቀላቀሉ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የታፈሱ ወጣቶች ከአካባቢው እያመለጡ በመውጣት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ይህንን የአስገዳጅ አፈሳ በመቃወም ወደ አዲስ አበባና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እየተሰደዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ጸረ ሰላም ባንዳዎች ከውጭ ጠላት ኃይል ጋር “ፅምዶ” በሚል ስም ኢትዮጵያን ለማዳከም በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቀሱት የስምረት ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ፤ ይህ የባንዳና የባዳ ቅንጅት አዲስ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጁ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ አስታውቀዋል።
ይህ ፅምዶ የተሰኘው ፕሮጀክት ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም አጥታ በተረበሸ ሁኔታ ውስጥ እንድትቆይ ማድረግ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የቀድሞው ሕወሃት ጽንፈኛ ቡድን ከሻዕቢያ ጋር ጥምረት በመፍጠር የዚሁ የትርምስ አጀንዳ ተላላኪና መሣሪያ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ስለሆነም የትግራይ ወጣቶች ህገወጥ ስልጣኑን ለማራዘምና ሀገር ለማተራመስ ከባዕዳን ኃይሎች ጋር ትስስር ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን የቀድሞ ሕወሓት ጽንፈኛ ቡድንን በቃ ማለት እንደሚገባቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።