AMN- ሰኔ 16/2018 ዓ.ም
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የዛሬ ሁለት ወር ያስጀመርነው የቅጠል ተራ የቤቶች ግንባታ በአስደናቂ ፍጥነት እየተሰራ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ ዛሬ የቤቶቹን ግንባታ ሂደት በሳይቱ በመገኘት መገምገማቸውን ገልጸዋል፡፡
የዛሬ ሁለት ወር የተጀመሩ ህንጻዎች 9ኛ ወለል ላይ መድረሳቸውን ተመልክተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች ፣ ቦታውን ከማጽዳት ጋር በተያያዘ የዛሬ ወር የተጀመሩ ህንጻዎችም 4ኛ እና 5ኛ ወለል ላይ የደረሱ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት የግንባታውን ሂደት ተመልክተን የጨመርናቸው ሶስት ህንጻዎችም ጅማሮ በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በፕሮጀክቶቹ የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ የንግድ፣ የጸጥታ፣ ትምህርት ቤት እና ጤና ተቋማት፣ የስፖርት ማዘዉተሪያ፣ የህፃናት መጫወቻ እና የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች እንዲሁም ሌሎች የህዝብ የጋራ መገልገያዎች እኩል ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ሲሉም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የምንገነባው መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ህጻናት ቦርቀው የሚያድጉበት፣ ወጣቶች የአካል እና የአዕምሮ ብቃታቸውን የሚያዳብሩበት፣ ዜጎቻችን አገልግሎቶችን በቅርበት የሚያገኙበት እና ክብራችንን የሚያስጠብቅ ምቹና ፅዱ አካባቢን ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ የቅጠል ተራ መኖሪያ መንደርን ትናንት ካስጀመርነው የገዳም ሰፈር እና በመሀሉ ላይ የሚገኘውን የጣልያን ሰፈር ጨምረን አገናኝተን በማልማት አካባቢውን የዘመነ አኗኗርና ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር አካባቢ እናደርገዋለን ሲሉም አክለዋል።

በምርጫ ወቅት ላይ ሆነን የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሳይቀዛቀዝ መቀጠሉ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ነዋሪዎቻችንን በታማኝነት የማገልገል አቋማችን ፅኑ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ህንጻዎቹን በጥራት እና በፍጥነት ገንብተው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየሰሩ የሚገኙ አመራሮቻችንን፣ ሰራተኞቻችንን፣ ማህበራትን፣ ተቋራጮችን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት አመሰግናለሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡