ኮሚሽኑ ጠንካራ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ለመሆን እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

You are currently viewing ኮሚሽኑ ጠንካራ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ለመሆን እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

AMN – ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠንካራ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ለመሆን እያደረገ ያለው ጥረት እና በአፈጻጸም ያሳየው ለውጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ኮሚሽኑ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሙሉ አቅሙ የታዛቢነት ሚናውን በተሳካ ሁኔታ መወጣቱ ተገልጿል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ27ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት የ11 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አድምጧል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት የተከናወኑ የክትትል ተግባራትን፣ ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎችን አቅርበዋል።

ተቋሙ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ትብብር በመፍጠር የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል።

ተቋሙ ከአውሮፓ ሕብረት፣ ከተለያዩ ኤምባሲዎች፣ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅት እና ከሌሎች ዓለም አቀፋዊና አህጉር አቀፍ ተቋማት ጋር ትብብሮችን በማጠናከር ስኬታማ ሥራ መሥራቱን ጠቅሰዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታችና የሰብዓዊ መብቶችን ያከበረ እንዲሆን ለማድረግ ኮሚሽኑ ስትራቴጂ ቀርጾ መንቀሳቀሱን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ባደራጃቸው የክትትል ቡድኖች አማካኝነት በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች በመንቀሳቀስ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫው ዕለት እና በድኅረ ምርጫ ሁኔታዎች ላይ የክትትል ሥራ አከናውኗል ብለዋል።

የኮሚሽኑን ከፍተኛ አመራር አባላት የያዘ ልዩ የክትትል ቡድን በማዋቀር የወቅታዊ ሁኔታዎች መከታተያ ሥርዓት ወደ ሥራ በማስገባት መረጃዎችን በፍጥነት ለማዕከል በማድረስ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረጉን ገልፀዋል።

የምርጫ ክትትል ግኝቱንም ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ሀገራዊ ምክክር መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን በማሳተፍ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አለመግባባቶችን እንዲሁም ልዩነቶችን በመፍታት በምክክር ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ ግንኙነትን ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን አመልክተው፤ በሂደቱም ሆነ በውጤቱ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፤ ኮሚሽኑ ጠንካራ ሀገራዊ ተቋም ለመሆን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በዓለም አቀፉ መድረክ ያገኘው የኤ(A) ደረጃ ተጠብቆ እንዲቆይ እና በቅርቡ በአፍሪካ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ያገኘው ተቀባይነት የሀገሪቷን መልካም ገጽታ የገነባና ሊበረታታ የሚገባው ስኬት ነው ብለዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር የመከታተያ ክፍል በማቋቋም ያደረገው የታዛቢነት ሚና አበረታች እንደሆነም አክለው ገልፀዋል።

ለሀገራዊ ምክክሩ ቀሪ ሥራዎች ስኬታማነት ኮሚሽኑ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚደነቅ ነውም ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የሚደረገው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ አሁንም መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

ሰብዓዊ መብትን የማክበር ባህልን ለመገንባት የሰብዓዊ መብት ትምህርቶች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በስርዓተ ትምህርት በማካተት ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።

በኮሚሽኑና በባለድርሻ አካላት መካከል የተጀመረው ገንቢ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review