የገነባናቸው የዲጂታል ማዕከላት የልህቀት ደረጃ በአፍሪካ ቀዳሚ ያደርገናል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማስፈን እየተገበራቸው ያሉ የዲጂታል መሶብ ማዕከላት፣ ከተማዋን በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ የልህቀት ማዕከል እያደረጓት እንደሚገኙ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት በአቃቂ ቃሊቲ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች የተገነቡትን 10ኛ እና 11ኛ የአዲስ መሶብ የዲጂታል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

በ2018 በጀት ዓመት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ማዕከላቱን የመክፈት ቃል ተገብቶ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች፣ ቃል የተገባውን በተግባር መፈጸም በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

አዳዲሶቹ የመሶብ ማዕከላት የተገነቡት አሮጌዎችን የመንግስት ቢሮዎች አሰራር በመቀየር፣ ዜጎች በአገልግሎት አሰጣጡ በራስ መተማመን እንዲሰማቸው በሚያደርግ ጥራት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አፅንኦት ሰጥተዋል።

ማዕከላቱ በአሰራራቸው ጥራት እና በሚሰጡት ፈገግታ የተሞላበት አገልግሎት መጎብኘት የሚችሉ መሆናቸውንም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

ማዕከላቱ ከተማ አስተዳደሩ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እና የተወሰኑ የፌዴራል መንግስት አገልግሎቶችን አቀናጅተው የሚሰጡ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጡ የትኛውም ዜጋ በየትኛውም ክፍለ ከተማ በመገኘት የሚፈልገውን አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል ነው።

ከንቲባዋ አክለውም፣ እኛ የገነባነው የክፍለ ከተማ ቅርንጫፎችን ሳይሆን የዲጂታል ማዕከላትንነው፤ ይህም በልህቀት ደረጃ በአፍሪካም ቀዳሚ ያደርገናል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሚፈለገው አጠቃላይ አገልግሎት 50 በመቶ የሚሆነው ወደ ዲጂታል መሶብ መገባቱን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፣ በቀሪው 50 በመቶ አገልግሎት ላይም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም አሁንም ባረጀው አሰራር ባሉ አገልግሎቶች ህዝቡ ለተወሰነ ጊዜ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል በግልፅ በመናገር፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የከተማዋ አስተዳደር ያለ ዕረፍት 24/7 እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review