AMN ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ምክር ቤት የንግድ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚመራቸውን ተቋማት የበጀት አመት የእቅድ አፈፃፀም እየገመገመ ነው፡፡
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ፤ በበጀት አመቱ ዘመናዊ የንግድ ስርዓትን በመገንባት እና የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ በኩል የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
የንግድ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጋቶች ዎር በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ ከተማ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ፤ “አዲስ አበባ ታምርት” እንዲሁም ዘመናዊ የንግድ ማዕከላትን በመገንባት ከተማዋን ከሸማችነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር ተችሏል ብለዋል።

የነዋሪውን የኑሮ ጫና በማቃለልና ገበያን በማረጋጋት ረገድም የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማስፋፋት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡
የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ አበረታች ለውጥ መመዝገቡንም ተናግረዋል።
የንግድ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ጉዳዮች ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ተቋማት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን ማከናወናቸውንም ገልፀዋል።
የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ፣ የስራና ክህሎት ቢሮ ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ፣ የቱሪዝም ኮሚሽን ፣ የአርሶአደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽንና የህብረት ስራ ኮሚሽን የ2018 በጀት አመት የዋና ዋና ተግባራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርታቸውን አቅርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
በደሳለኝ ሙሐመድ