AMN ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
ፐብሊክ ሰርቪስ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመሆን በሚሰራው “የአገልጋይ” ፕሮግራም 89 በመቶ የሚሆኑ ቅሬታዎችን መፍታት ተችሏል ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2018 ዓ.ም የአስፈፃሚ አካላት ማጠቃለያ ሪፖርትን ያዳመጠ ሲሆን የተለያዩ ተቋማት የአመቱን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እና ቀጣይ የሥራ ዕቅዶችን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር)፤ በበጀት ዓመቱ የሰራተኞች እርካታን ከ63 በመቶ ወደ 70 በመቶ ከፍ ማድረግ ስለመቻሉ አንስተዋል፡፡

እንዲሁም በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አማካኝነት የተገልጋይ እርካታን ወደ 76 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ፐብሊክ ሰርቪስ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በጋራ በመሆን በሚሰራው “የአገልጋይ” ፕሮግራም 89 በመቶ የሚሆኑ ቅሬታዎችን መፍታት ተችሏልም ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የመልካም አስተዳደር የሥራ እንቅስቃሴዎችን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን አማራጮች ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ለቀጣይ ትውልድ ምስክር ይሆን ዘንድ የቀደመ የመዲናዋን ገፅታ ሰንዶ ከማስቀመጥ አንፃር ውጤታማ ስራ መስራቱን የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐፍታይ ገብረእግዚያብሔር ናቸው።
በተለይም ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመሆን በሚሰራው “ዋርካ” የቴሌቭዥን ፕሮግራም
ህዝቡ ከአመራሮች ጋር በቀጥታ በመገናኘት ችግሮችን የሚያነሳበት እና የሚሞግትበትን መድረክ መፍጠር መቻሉን በዚህም በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስለመፈታታቸው አንስተዋል።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በ2018 በጀት ዓመት የከወናቸውን አበይት ስራዎችን በማንሳት ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችንም ጭምር ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ ናቸው።
በሪፖርታቸውም ጣቢያው ከ30 ከሚልቁ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት በመፈፀም ሙሉ ተዓማኒና ተደራሽ መረጃን በተለያዩ አማራጮች እያቀረበ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡
ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሁነትችን ከመዘገብ ባሻገር የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በመስጠትም ጭምር ሰፊ ስራዎች ስለመሰራታቸው ገልፀዋል።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሀይማኖታዊ እና የአደባባይ በዓላትም ይዘታቸው እና መልዕክታቸው ሳይጎደል በሁሉም አማራጮት ተደራሽ በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እንደያዘም በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ የፍትህ ቢሮ እንዲሁም የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣንም በተመሳሳይ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአመቱን አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።
በትባረክ ኢሳያስ