AMN- ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
ዜጋ- ተኮር ዲፕሎማሲን ማዕከል ያደረገው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስኬታማ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሀገር የክብር መገለጫ ነው በሚል የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ መንግሥት ጠንካራ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሪያድ የሚገኘውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚሲዮን እና በጂዳ የሚገኘውን ቆንስላ ጽሕፈት ቤት በማስተባበር የተከናወነው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ፍሬ አፍርቷል።
በሳዑዲ ዓረቢያ ለእስር ተዳርገው የነበሩ 1 ሺህ 655 ኢትዮጵያውያን ዜጎች የፍርድ ሂደታቸው እንዲቋረጥና የምሕረት አዋጅ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።

ከእነዚህ የምሕረት አዋጅ ከተደረገላቸው መካከልም የመጀመሪያዎቹ 320ዎቹ ኢትዮጵያውያን ትናንት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ይህ ስኬት መንግሥት በለውጡ ዓመታት የሰውን ልጅ ክብርና ጥቅም ማዕከል ያደረገ አሰራር መዘርጋቱን የሚያመላክት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪና በከፋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ ሰፊ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ ከለውጡ ወዲህም በተለያዩ ሃገራት በከፋ ሁኔታ ላይ የነበሩ ከ432 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
መስከረም 2018 ዓ.ም በተጀመረው ልዩ የተቀናጀ ሥራ እስካሁን ባለው መረጃ ከ77 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ አገር ቤት መመለስ ተችሏል።
ተመላሾችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተቀናጀ ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ ሲሆን ለተመላሾች የስነ-ልቦና እና የሕክምና ድጋፍ በማድረግ ወደ ስራ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠረ ነው።

ሕገ-ወጥ ስደትን ለመግታት ቤደረጃው የግንዛቤ መፍጠርና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ዜጎች የሁለትዮሽ ስምምነት በተደረገባቸው ሃገራት በሕጋዊ መንገድ ተሰማርተው እንዲሰሩ ሥርዓት መዘርጋቱ ይታወሳል፡፡
በትዝታ መንግስቱ