AMN – ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ለማልማት እና የደን ሽፋንን ለማሳደግ ታስቦ በ2011 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፤ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
መላውን ሕዝብ በአንድ ዓላማ ሥር ያሰባሰበውና ላለፉት ስምንት ዓመታት የቀጠለው ይህ ግዙፍ ሀገራዊ ንቅናቄ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ እውቅና እና አድናቆት ካገኘችባቸው መርሐ ግብሮች መካከል ግንባር ቀደሙ ለመሆን በቅቷል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ትብብርና ንቁ ተሳትፎ 48 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ እና አስደማሚ አሻራ ማሳረፍ ተችሏል።
ዘንድሮም ይህንን ስኬት ይበልጥ ለማሳደግ የ8 ቢሊየን ችግኞች ተከላ ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯል።

ይህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወነው አረንጓዴ ልማት በዋና ከተማዋ አዲስ አበባም ደምቆ የታየ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ዘመቻዎች 90 ሚሊየን ችግኞች ተተክለዋል።
ይህ አጠቃላይ ጥረት የሀገሪቱን የደን ሽፋን እጅግ ዝቅተኛ ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማድረስ ያስቻለ ታላቅ ታሪካዊ ስኬት ነው።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው አረንጓዴ የለበሱ ሲሆን አዲስ አበባን ንፁህ፣ ውብ፣ ለመኖር ምቹ እና የቱሪስት ማዕከል የማድረግ እቅድን እያሳካ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪም ከተተከሉት ችግኞች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ለምግብነትና ለገቢ ምንጭነት የሚውሉ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች፣ የቡና ችግኞች እንዲሁም ለንብ ማነብ ሥራ የሚውሉ ዕፅዋት በመሆናቸው ለዜጎች ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅምና የምግብ ዋስትና መፍጠር ተችሏል።
የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በከተማ ደረጃ 6 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የታቀደው ንቅናቄ በይፋ የተጀመረ ሲሆን ይህም ከተማዋ የልምላሜና የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን የሚደረግ ሌላው ታሪካዊ እርምጃ ነው።

ይህ ግዙፍ ንቅናቄ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ሕያው ቅርስ በመሆኑ የተመዘገቡት ስኬቶች ይበልጥ ቀጣይነት እንዲኖራቸው እያንዳንዱ ዜጋ ከችግኝ ማፍላት ጀምሮ እስከ መትከልና መንከባከብ ድረስ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች በወንዝ ዳርቻ፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤትና በሐይማኖት ተቋማት፣ በግል ይዞታዎችና በጎዳናዎች ላይ ለምግብነት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን፣ የጥላና የውበት ዛፎችን በመትከል የበኩላቸውን ዐሻራ ሊያሳርፉ ይገባል።
በበረከት ጌታቸው