ዛይድ የደግነት ሩጫ የ5 ኪ.ሜ ውድድር መካሄድ ጀመረ

You are currently viewing ዛይድ የደግነት ሩጫ የ5 ኪ.ሜ ውድድር መካሄድ ጀመረ

AMN – ሚያዝያ 25/2018 ዓ/ም

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መስራች የሆኑትን የሼህ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያንን ሰብአዊ ራዕይ መነሻ በማድረግ የሚዘጋጀው ታዋቂው ዛይድ የደግነት ሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው የበጎ አድራጎት ሩጫ ውድድሩ “ዛይድ የድግነት ሩጫ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአቡ ዳቢ፣ በኒው ዮርክ እና በካይሮ ከተሞች ሲካሄድ የነበረውን ይህንን ታላቅ ዓለም አቀፍ ሩጫ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደች ሲሆን፣ የዛሬው ሩጫ ውድድርም በርካታ ቁጥር ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በከፍተኛ ድምቀት ተጀምሯል።

አምስት ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው በዚህ የሩጫ ውድድር ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሯጮች ፣ ታዋቂ አትሌቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ህጻናት እና የውጭ ሀገራት ዜጎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ውድድሩ በተጀመረበት ወቅት የተስተዋለው ከፍተኛ መነቃቃትና ደስታ፣ ስፖርታዊ ጤንነትን ከማስፋፋት ባለፈ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት እና የበጎ አድራጎት አንድነት መንፈስ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ታይቷል።

ከዚህ ታላቅ የሩጫ ውድድር የሚሰበሰበው ገቢ በሙሉ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት እና የበጎ አድራጎት ስራዎች የሚውል ሲሆን፣ በተለይም ውድድሩ በከፍተኛ ወጪ የሚከናወኑ የካንሰር ህክምናዎችን ለመደገፍ፣ የኩላሊት እጥበት ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እገዛ ለማድረግ እንዲሁም አዳዲስ የህክምና ምርምሮችን ለማገዝ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህንን የታሪክ ምዕራፍ በጀግና ሯጮች ምድር ከማከናወን ባሻገር ለውድድሩ አሸናፊዎች ለእያንዳንዳቸው ከ500 ሺህ ብር በላይ የሽልማት ገንዘብ የሚበረከት ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ በ 5ኪ.ሜ. ውድድር የተመደበ ከፍተኛው የገንዘብ ሽልማት ነው ተብሏል።

ዛይድ የደግነት ሩጫ 5 ኪ.ሜ ሩጫው በአዲስ አበባ መካሄዱ ውድድሩ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት ይበልጥ የሚያጠናክር ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ማህበራዊ እና ሰብአዊ ድጋፍ ይበልጥ የሚያሳይ እንደሆነም ተገልጿል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review