AMN – ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀውን የታሪክና የፖለቲካ ግጭት አዙሪት በዘላቂነት ለመፍታት፣ አካታች ብሔራዊ ምክክር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን የሰላምና ደኅንነት መምህርና ተመራማሪ አቶ አሌክስ ብርሃኑ ገለጹ።
ተመራማሪው ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስገነዘቡት፤ ምክክር ማለት በሁሉም ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት ሐሳብና እምነት መያዝ ሳይሆን ልዩነቶችን በአግባቡ ማስተናገድ የሚችል ጠንካራ ሥርዓትና የጋራ ዕሳቤ መፍጠር ነው።
ብሔራዊ ምክክር የጋራ እውነትን መፍጠሪያ እንጂ አንድ ዓይነት አስተሳሰብን በኃይል መጫኛ ሥርዓት አለመሆኑንም አብራርተዋል።
ሰዎች የተናጠል እውነት ያላቸው በመሆኑ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ ትልቁን ሀገራዊ ምስል መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ ዘላቂ የሆነ የጋራ እውነት ሊኖር እንደማይችልም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በታሪካችን ውስጥ በተግባባንባቸው ዘመናት ልዩነቶቻችንን ከአገር ሕልውና በታች በማስገዛታችን እንደ ዓድዋ ድል እና እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ታላላቅ ብሔራዊ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አቶ አሌክስ አስታውሰዋል፡፡

በአንጻሩ ግን ባልተግባባንባቸውና መለስተኛ ልዩነቶችን ማቻቻል ባቃተን ዘመናት ሀገሪቱ ለከፋ የፖለቲካ ቀውስ፣ ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀል እና ለተቋማት መዳከም መዳረጓን በዝርዝር አስረድተዋል።
ምክክር የሚቀጥለውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ የመወሰኛ ታሪካዊ መድረክ ነው ያሉት ተመራማሪው፣ ብሔራዊ ምክክሩ እንዲሳካና የጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዲቀረጽ ከግለሰብ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት አካል ድረስ የግልና የቡድን ፍላጎትን መተው ወይም በውይይት ማቻቻል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ታጣቂ ኃይሎች ነፍጥንና መሣሪያን ወደ ጎን አድርገው፣ ያነሷቸው ጥያቄዎች በንግግርና በውይይት ሊፈቱ እንደሚችሉ እምነት በመጣል ለሰላም ዕድል ሊሰጡ እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ አሌክስ፣ የፖለቲካ ልሂቃንም የጥላቻና የንትርክ ማስፈጸሚያ መሆንን አቁመው ለጋራ እውነትና ለሀገር አንድነት ሊገዙ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያን ካለፈው ታሪካቸው ተምረው በልዩነቶቻቸው ላይ በሰለጠነ መንገድ መነጋገር እንደሚገባቸው የገለጹት ተመራማሪው፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ከመጋበዝ ይልቅ ሀገሪቱን ቀደም ሲል ከገባችበት የግጭት አዙሪት ማውጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውጤታማ ምክክር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በበረከት ጌታቸው