የመደመር ዕሳቤ እና የኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲስ ምዕራፍ

You are currently viewing የመደመር ዕሳቤ እና የኢትዮጵያ ቱሪዝም አዲስ ምዕራፍ

AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም

የመደመር ዕሳቤ በኢትዮጵያ በፖለቲካና በምጣኔ ሀብት ዘርፎች ላይ አዲስ አቅጣጫ የቀየሰ ፍልስፍና ሲሆን ፣ በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛና መዋቅራዊ ለውጥ አምጥቷል።

ዕሳቤው ያለፈውን ታሪክና ቅርስ ከአዲስ እይታና ልማት ጋር ማቀናጀትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ፣ የሀገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች በማስፋትና የገጽታ ግንባታ ስራዎችን በማዘመን ረገድ በርካታ ለውጦችን አስገኝቷል፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ቱሪዝም በአብዛኛው ታሪካዊ በሆኑት የሰሜኑ መስመሮች ማለትም፣ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ባህላዊ በሆነው የደቡብ መስመር ላይ ብቻ የተወሰነ ሲሆን፣ የመደመር እሳቤ ይህንን እይታ ቀይሮታል፡፡

በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ አድርጓል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ የተገነቡት የሸገር፣ የእንጦጦ፣ የወዳጅነት፣ የሳይንስ ሙዚየምና የዓድዋ መታሰቢያ ፕሮጀክቶች ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ብቻ ሳይሆን፣ ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ የቱሪዝም ማዕከል አድርገዋታል።

“ገበታ ለሀገር” እና “ገበታ ለትውልድ” በሚሉ ሀገራዊ ጥሪዎች አማካኝነት በደቡብ እንደ ኮይሻ፣ በአማራ ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ወንጪ እንዲሁም እንደ ሃላላ ኬላ ያሉ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቦታዎች ወደ ትላልቅ የቱሪስት መስህብነት ተቀይረዋል።

የመደመር ፍልስፍና አንዱ ምሰሶ ቅንጅት በመሆኑ፣ የቱሪስት መዳረሻዎች ብቻቸውን ሳይሆን፣ ከመሰረተ ልማት ጋር ተሳስረው እንዲለሙ ተደርጓል። ወደ አዳዲሶቹ የቱሪስት ማዕከላት የሚወስዱ ዘመናዊ መንገዶች፣ የቴሌኮም አውታሮችና የኤሌክትሪክ አቅርቦቶችም አብረው ተገንብተዋል።

የአየር መንገድ ትስስርን በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሀገር ውስጥ በረራዎች ከአዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ጋር የማቀናጀት ስራ ተሰርቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ቱሪዝም ሲባል በቀጥታ ከውጭ ሀገር የሚመጡ ጎብኝዎችን ብቻ የመጠበቅ ዝንባሌ እንደነበር በማንሳት፣ የመደመር ዕሳቤ ግን “ሀገርን ማወቅ” እና “የራስን ማድነቅ” በሚል እሴት የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲነቃቃ ማድረጉን መግለፃቸው ይታወሳል።

በዚህም ኢትዮጵያውያን በዓላትንና የዕረፍት ጊዜያትን በሀገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዲያሳልፉ ትልቅ መነሳሳት መፈጠሩን አንስተዋል። ይህ መነሳሳት የውጭ ምንዛሬ እጥረት በሚኖርበት ወይም የፖለቲካ አለመረጋጋቶች እና እንደ ወረርሽኝ መከሰት ያሉ ዓለም አቀፍ ቀውሶች በሚከሰቱበት ጊዜ የቱሪዝም ዘርፉ ሙሉ በሙሉ እንዳይጎዳ ትልቅ ደጋፊ ምሰሶ ይሆናል።

የመደመር ዕሳቤ የኢትዮጵያን ገጽታ ከረሃብና ጦርነት ትረካዎች አውጥቶ ፣ በአረንጓዴ ልማትና በዘመናዊ ስልጣኔ ላይ ወደተገነባ አዎንታዊ ገጽታ ለመቀየር ቱሪዝምን እንደ ዋነኛ መሳሪያ ተጠቅሞበታል።

ታዋቂ የዓለም መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ጊዜ በእነዚህ አዳዲስ የቱሪስት መስህቦች ለምሳሌ አንድነት ፓርክን እንዲጎበኙ በማድረግ የሀገር ገጽታ ግንባታ ስራው ውጤታማ እንዲሆን ተደርጓል።

ቱሪዝም የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን የብዙሃኑን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንዲሆን ተደርጓል። በአዳዲሶቹ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዙሪያ የሚኖሩ የአካባቢው ማህበረሰቦች በቅርሶች ጥበቃ፣ በግብርና አቅርቦት እና በእደ-ጥበብ ሥራዎች በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ፈጥሯል።

የግሉ ዘርፍ በሆቴል፣ በሎጅና በቱር ኦፕሬተርነት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

በአጠቃላይ፤ በመደመር ዕሳቤ ስር የቱሪዝም ዘርፍ ከባህላዊና ከተወሰኑ ቦታዎች እይታ ወጥቶ፤ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ፣ የከተሞች ውበት መገለጫ፣ የሀገር ገጽታ መገንቢያ እና የማህበረሰብ የሥራ እድል ፈጣሪ እንዲሆን ስትራቴጂያዊ ለውጥ ተደርጎበታል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review