የዚምባብዌው ዛኑ-ፒኤፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ለብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልክት አስተላለፈ

AMN ሰኔ 25/2018

የኢትዮጵያ 7ኛው አጠቃላይ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ፥ ከእህት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች የሚላኩ ይፋዊ የእንኳን ደስ አላችሁ መግለጫዎች እና ደብዳቤዎች መላካቸውን ቀጥለዋል።

ይህ ሰፊ የዓለም አቀፍ እውቅና አገሪቱ ያስመዘገበችውና የደረሰችበት ወሳኝ የዲሞክራሲ ምዕራፍን የሚያንጸባርቅ ሁኗል።

የዚምባብዌ አፍሪካ ብሔራዊ ህብረት-የአርበኞች ግንባር (ZANU-PF) ምርጫው በስኬት በመጠናቀቁ ምክንያት ለብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ለብልጽግና ፓርቲ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ዛኑ-ፒኤፍ (ZANU-PF) ባስተላለፈው መልዕክት የኢትዮጵያ ምርጫ በስኬት መጠናቀቅ አገሪቱ ለሰላም፣ ለመረጋጋት እና ለሕዝቦቿ ሉዓላዊ ፈቃድ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ የዲሞክራሲ ምዕራፍ ነው ሲል ገልጾታል።

ፓርቲው አክሎም ብልጽግና ፓርቲ ያገኘው ሰፊ የሕዝብ ውክልና ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራር እንዲሁም አካታች ልማትን፣ ብሔራዊ አንድነትንና ቀጣናዊ ውህደትን ለማምጣት ባላቸው ራዕይ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ መሆኑን አመልክቷል።

በሁለቱ እህት ፓርቲዎች እና አገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የገለጸው ዛኑ-ፒኤፍ (ZANU-PF)፤ ኢትዮጵያ አፍሪካ የራሷን ዕድል በራሷ ለመወሰንና የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማግኘት ለምታደርገው ጥረት ታማኝ አጋር መሆኗን ገልጿል። በተጨማሪም የዚህ ምርጫ ስኬት የፓን-አፍሪካኒዝም አብሮነትን እንደሚያጠናክርና የአፍሪካ ኅብረት የ2063 አጀንዳ የጋራ ግብን እንደሚያሳይ አጽንኦት ሰጥቷል።

በጨረሻም ሁለቱ ፓርቲዎችና አገራት ለሕዝቦቻቸው ብልጽግና፣ አንድነት እና ክብር በጋራ መስራታቸውን ይቀጥላሉ ሲል የገለጸው ፖርቲው በመካከላቸው ያለውን የወንድማማችነት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርም ዛኑ-ፒኤፍ (ZANU-PF) ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review