AMN ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያለው፣ በታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች ላይ የተመሠረተ ነው። ሃገራቱ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ ወዳጅነት አላቸዉ።
የሁለቱ ሃገራት ኦፊሴላዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት 125 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን ግንኙነታቸውም በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተመሠረተ ነዉ። ሃገራቱ በሁለትዮሽ፣ በክልላዊ እና በአለም አቀፍ መድረኮች አብረው ይሰራሉ።
በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላቸው የጋራ አቋም የሁለቱን ሃገራት ጠንካራ ግንኙነት የሚያረጋግጥ ነዉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የጋራ ጥቅም ላይ ያተኮሩ የሥራ ጉብኝቶችን በማድረግ የግንኙነታቸዉን ደረጃ ከፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የሩሲያዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸዉም የሁለቱ ሃገራት ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት ጠንካራ መሠረት ላይ ለመቆሙ ትልቅ ማሳያ ነዉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፥ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና የአሜሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር መለስ ዓለም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢነርጂና ቴክኖሎጂ: ንግድና ኢንቨስትመንት: በትምህርትና የባህል ልውውጥ ዘርፍ በትብብር በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በተለይ ኢትዮጵያ የBRICS አባል ሃገራትን መቀላቀሏን ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። በአጠቃላይ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በመግባባት ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም በላይ በጋራ የልማት ግቦች ላይ ያተኮረ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን የሁለቱን ሃገራት ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስመልክቶ በአዲስ አበባ በየዓመቱ በሚከበረው የሩሲያ ቋንቋ ቀን ላይ እንደተናገሩት: በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት በሁሉም መስክ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ማረጋገጣቸዉ ይታወሳል።
በወንድማገኝ አሰፋ