መንግሥት ለሰላም የዘረጋው እጅ ውጤት እያመጣ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing መንግሥት ለሰላም የዘረጋው እጅ ውጤት እያመጣ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስብሰባው ላይ በመገኘት፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ ሰላምን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና አስተማማኝ መረጋጋትን ለመፍጠር መንግስት እያከናወናቸው ያሉትን አበይት ተግባራትና የተመዘገቡ ስኬቶችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡

ሰላምን ለማስፈን በተሰሩ የተቀናጁ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ሰላም አንፃራዊ በሆነ መልኩ መሻሻሉን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታትና ጸጥታን ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ጦርነት ብቻውን ወደ ድል አይወስድም፤ ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለው ሕዝብን በተከታታይነት በማወያየትና ቅሬታዎቹን በነጻነት አውጥቶ እንዲነጋገር ማድረግ ሲቻል መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ባለፉት ዓመታት የተረጋጋ ፖለቲካዊ አውድ ለመፍጠርና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

መንግሥት ለሰላም የዘረጋው እጅ ውጤት እያመጣ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ውስጥ ይንቀሳቀሱ ከነበሩት የታጠቁ ኃይሎች መካከል በርካቶቹ በመንግሥት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተከትለው፣ ተደራድረውና መሣሪያቸውን አስቀምጠው ወደ ሰላም መመለሳቸውንም አስረድተዋል፡፡

ጦርነትና ግጭት ወደ ሰላማዊ ጉዞ እንደማይወስድና ሀገርን ለማፅናትም እንደማይበጅ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁንም በጫካ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን ተጠቅመው በጋራ ሀገር እንዲገነቡ መንግሥት የሰላም ጥሪውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review