AMN – ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም
በትናንትናው ዕለት በቡድን ተከፋፍለው መመካከር የጀመሩት ተመካካሪዎች ዛሬም በየቡድናቸው በመሆን መመካከር መቀጠላቸው ተገልጿል፡፡
50 ተመካካሪዎችን በመያዝ በ80 ቡድን ተከፋፍለው መመካከር የጀመሩት ንዑሳን ቡድኖች በተሟላ ሁኔታ ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ በየንዑስ ቡድናቸው አስር አስር በመሆን ምክክር በማድረግ ላይ እንደሚገኙና ይህ ሂደት እስከ ነገ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በዚህ ሂደት ተመካካሪዎች በሚመካከሩባቸው የአጀንዳ ሃሳቦች ላይ በርካታ ሃሳቦችን እና ምልከታዎችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ሂደቱ ተመካካሪዎች ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ አመለካከቶችን እና ምክንያቶችን ከስር መሰረቱ አንዳቸው ሌላቸውን እንዲረዱ መደላድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል ብሏል፡፡
ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ ተቋማት በሙያቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው እና ለአጀንዳ ሃሳቦቹ ባላቸው ሙያዊ ቅርበት ብቁ ናቸው ብሎ ያመነባቸው 80 የሚጠጉ የባለሙያዎች ስብስብ (Panel of Experts) በማሰባሰብ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ እያሳተፈ እንደሚገኝም ጠቅሷል፡፡

የባለሙያዎች ስብስብ በአጀንዳ ነጥቦች ላይ ለሚፈጠሩ ብዥታዎች ማብራሪያ በመስጠት ሂደቱን በመደገፍ ላይ እንሚገኙም አብራርቷል፡፡
ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት፣ ከተለያዩ የሙያ ማህበራት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ እና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተውጣጡ ከ50 በላይ ገለልተኛ ታዛቢዎች የምክክር ሂደቱን እየታዘቡ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ባወጣው መረጃ ገልጿል፡፡