በታሪካዊዉ ሃገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ የተወለደዉ ልጅ – “ኮሚሽን” ተብሎ ተሰየመ

AMN ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

በሀገራዊ ምክክሩ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተሳተፈች ያለችው ወ/ሮ ሀዳ አልማህዲ ወንድ ልጅ በሰላም የተገላገለች ሲሆን ስሙንም “ኮሚሽን” ብላዋለች።

ባሳለፍነው ሳምንት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በመሳተፍ ላይ የነበረች የጋምቤላ ክልል ተወካይዋ ወ/ሮ ክርኑዶ ኡጁሉ ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላ ስሙም ምክክር መባሉ የሚታወስ ነው።

በዚህ ምክክር ጉባኤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣችው የጉባኤው ተሳታፊ ወ/ሮ ሀዳ አልማህዲ አዲስ አበባ በሚገኜው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ወንድ ልጅ በሰላም የተገላገለች ሲሆን ይህም በምክክር ሂደቱ ሌላው አስደናቂ ክስተት ሆኗል ።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኡራ ወረዳ በምክክሩ ላይ እየተሳተፈች ያለችው ይህችው እናት የመውለጃ ጊዜዬ እየደረሰ መሆኑን ባውቅም ለኢትዮጵያዊያን አብሮነትና ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም በጋራ በሚመከርበት በዚህ ጉባኤ መሳተፍ አለብኝ በሚል አቋም መገኘቷን አስታውቃለች ።

የጉባኤው አጀንዳዎች ላይ ለሀገራችን ይበጃል የምትለውን ሀሳብ በመስጠት ንቁ ተሳትፎ ስታደርግ መቆየቷን የገለጸችው ወ/ሮ ሀዳ አልማህዲ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ልጇን በመገላገሏ መደሰቷን ገልጻለች ።

በዚህ ታሪካዊ ሁነት ላይ የተወለደውን ልጇን ስም “ኮሚሽን ” ያለችው ወ/ሮ ሀዳ የምክክሩ ተሳትፎዋን እንደምትቀጥል አሳውቃለች።

ይህ ምክክር አንድነታችን የሚጠናከርበት እና ሀገራችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግር ይሆናል የሚል ዕምነት እንዳላትም ጠቁማለች።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review