AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
እንደ ቻይና ፣ ጃፓን ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ጀርመን ያሉ ሃገራት በዓለም ላይ ጠንካራ የሥራ ባህል በመገንባት የሚታወቁ ሲሆኑ ዛሬ ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እስከማስመዝገብ ደርሰዋል፡፡
በእነዚህ ሃገራት የሚኖሩ ዜጎች ማንኛውንም ሥራ በማክበር በቁርጠኝነትና በትጋት ለረጅም ሰዓት በመስራት፤ በትምህርት እና በስራ ቦታ ከፍተኛ የሆነ የውድድር መንፈስ፤ በህብረተሰቡ ውስጥ ባላቸው የሥራ ፍቅር ይታወቃሉ፡፡
የሥራ ሰዓት ማክበር፣ በሥራ ሰዓት ሙሉ ትኩረትን ሥራ ላይ ማድረግ፣ በቡድን መስራት፣ ፈጠራና ሙያዊ ክህሎትን ማዳበር፣ በእቅድ ብቻ መስራት፣ የሥራ እና የግል ሕይወት ሚዛንን መጠበቅ ሃገራቱ ከገነቡት ጠንካራ የሥራ ባህል መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሃገራቱ ጠንካራ የሥራ ባህል መገንባታቸውን ተከትሎ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ የማይደፈር ወታደራዊ ተቋም፣ተወዳዳሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም እና ሌሎች እድገቶችን መፍጠር ችለዋል፡፡
በኢትዮጵያም ከባህልና ከሐይማኖት አንጻር ሥራ ክብር እንዳለው ቢታመንም ጠንካራ የሥራ ባህል ከመገንባት ረገድ ግን በርካታ ውስንነቶች መኖራቸውን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ከቀደመው ዘመን ጀምሮ ሲወርድና ሲዋረድ በመጣው አሉታዊ እሳቤ ምክንያት የሚሰራ ሰው የሚከበርበትና የተሻለ እድገት የሚያገኝበት አግባብ አልነበረም፡፡
ይልቁንም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ግለሰቦችን የማያበረታቱ አሉታዊና የንቀት መጠሪያዎች ሲወጣላቸው ቆይቷል፡፡
ለረጅም ሰዓት ጠንክሮና በርትቶ የሚሰራ፣ የሥራ ሰዓት የሚያከብር፣ታዛዥ እና ሥነ ምግባር ያለው ሰራተኛ የሚከበርበት ሳይሆን እንደ ባሪያ የሚታይበት ሁኔታ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንኑ የሥራ ባህል አስመልክቶ በመደመር መጽሃፋቸው እንዳሰፈሩት፤ በሽመና ሥራ ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች “ቁጢት በጣሽ” የሚል ስያሜ ይወጣላቸው ነበር፡፡
የብረታ ብረት ባለሙያዎች “ቀጥቃጭ” የሚል የንቀት ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ገበሬው አፈር ገፊ፤ ነጋዴው መጫኛ ነካሽ ተብሎ በመሰደቡ ምክንያት የሥራ ባህል በማህበረሰቡ ውስጥ እንዳይጎለብት ትልቅ ምክንያት ሆኗል፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ግን ከኢትዮጵያ እኩል የሸክላና “ፖርሲሊ” የሥራ ባህል የነበራቸው የሩቅ ምስራቅ ሃገራት ዛሬ ላይ በዚህ ሞያ የዓለምን ገበያ ተቆጣጥረውታል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራና ሰራተኛን የመናቅ ባህል ከየት መጣ? እስከ ዛሬ ድረስ ሥራንና ሰራተኛን የመናቅ ኋላ ቀር አመለካከትስ ምን ያህል ተሻሽሏል? የሚለው ጥያቄ ትልቅ ምላሽ ይፈልጋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር መጽሃፋቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጦርነትና ለጦረኝነት የሚሰጠው እና ለሥራና ለሰራተኛ የሚሰጠው ቦታ እኩል አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ለጦርነትና ለጦረኝነት የሚሰጠው ቦታ ዳር ድንበርና የሃገር ሉአላዊነትን ለማስከበር ቢጠቅምም በደም መስዋዕትነት ብቻ የበለጸገችና ጠንካራ ሃገር መገንባት አልተቻለም፡፡
ስራን በሚንቀው እሳቤ ምክንያት ከእንስራ ይልቅ እንዝመት እና እንዝረፍ የሚለው አመለካከት ባህል እየሆነ መምጣቱ ለሃገራዊ ሰላምና ደህንነት እንቅፋት እስከመሆን ደርሷል፡፡
ዛሬ ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ሥራ የማይሰሩ፣ ሥራን የሚንቁና የሚሰራን ሰው የሚሰድቡና የሚንቁ ግለሰቦች መኖራቸውም ከዚሁ ከኋላ ቀር እሳቤ የሚመነጭ ነው፡፡
ኋላ ቀሩ እሳቤ ስራን የሚንቅ እና እንዝመትን የሚያስቀድም ብቻ ሳይሆን በንግግርና በምክክር የማያምን ጭምር በመሆኑ የጸጥታ ችግር ከመፍጠር አልፎ የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት መለወጥ አልቻለም፡፡
ለመሆኑ ልዩነቶችን በመነጋገር የሚፈታ ማኅበረሰብ መፍጠር ለምን ተሳነን? ለሁሉም ነገር መፍትሔውን ጦርና ጦረኝነት አድርገን የምንቀጥለውስ እስከመቼ ነው?
በወንድማገኝ አሰፋ