የአትሌት ሻምበል ባሻ የብርጓል መለሰ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ

You are currently viewing የአትሌት ሻምበል ባሻ የብርጓል መለሰ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ

AMN- ግንቦት 6/2018 ዓ.ም

የአትሌት ሻምበል ባሻ የብርጓል መለሰ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡

አትሌት ሻምበል ባሻ የብርጓል መለሰ ከአባቷ ከአቶ መለሰ አራጌ እና ከእናቷ ሙልዬ ሙላቴ መጋቢት 8 ቀን 1982 ዓ.ም በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ልዩ ስሙ ገረገራ ከተማ የተወለደች ሲሆን በነበራት ልዩ የስፖርት ተሰጥኦ እና ፍላጎት በ1999 ዓ.ም የሩጫውን አለም ተቀላቅላለች።

ሻምበል ባሻ አትሌት የብርጓል መለሰ በ2003 ዓ.ም የመከላከያ መቻል ስፖርት ክለብ አባል ሆና ተቀላቅላለች። ክለቧን ወክላ በተወዳደረችባቸው የሀገር ውስጥ ውድድሮች በተለይም በ10 ኪሎ ሜትር በጃንሜዳ ሀገር አቋራጭ ውድድር፣ በአዲስ አበባ ክለቦች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ፣ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እንዲሁም በሌሎችም የጎዳና ውድድሮች ላይ አብዛኛውን ውድድሯን በአንደኝነት በማጠናቀቅ ለክለቧ መቻል አኩሪ ገድል አስመዝግባለች፡፡

ጀግናዋ አትሌት ሻምበል ባሻ አትሌት የብርጓል መለሰ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመታቀፍ በአለም አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ የሀገሯን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርጋ እንዲውለበለብ አድርጋለች። እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ኮንጎ ብራዛቢል በተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በግማሽ ማራቶን ተወዳድራ የነሀስ ሜዳሊያ እ.ኤ.አ በ2013 ፖላንድ በተካሄደው የአለም ሀገር አቋራጭ ውድድር በሴቶች በ10 ኪ.ሜትር የቡድን ውጤት የብር ሜዳሊያ አስመዝግባለች።

የመቻሏ አትሌት ሻምበል ባሻ አትሌት የብርጓል መለሰ በግል ባካሄደቻቸው ውድድሮች በረጅም ርቀት ሩጫ በርካታ ድሎችን አስመዝግባለች እ.ኤ.አ በ2015 ሂውስተን ማራቶን፣ ፕራግ ማራቶን፣ ችጋጎ ማራቶን እ.ኤ.አ 2018 ሻንጋይ ማራቶን ሪከርድ በማሻሻል ሊዝበን ግማሽ ማራቶን በአንደኝነት ያጠናቀቀች ሲሆን ፓሪስ ማራቶን እና ፍራንክፈርት ማራቶን ሁለተኛ የወጣችባቸው ናቸው ዱባይ ማራቶንን ሶስተኛ በመውጣት ሁለት ጊዜ ያሸነፈችባቸው ከብዙ በጥቂቱ አኩሪ ውጤቶቿ ናቸው፡፡

የመቻሏ አትሌቷ ሻምበል ባሻ የብርጓል መለሰ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም በካናዳ ኦታዋ ማራቶን ለሚደረገው ውድድር ለመሳተፍ ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም በጃል ሜዳ ልምምዷን እየሰራች እያለች ድንገት ዝልፍልፍ ብላ ስትወድቅ ባለቤቷን ጨምሮ ጓደኞቿ ህይወቷን ለማትረፍ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ቢወስዷትም ህይወቷ ሊተርፍ አልቻለም።

የቀብር ስነ ስርዓቷም በዛሬው እለት ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ቤተሰቦቿ ወዳጅ ዘመዶቿ የመከላከያ ሠራዊት አመራር እና አባላት በተገኙበት በመከላከያ የክብር ዘብ እና ማርሽ ባንድ በመታጀብ ተፈፅሟል፡፡

ሻምበል ባሻ አትሌት የብርጓል መለሰ ከአትሌት ወሰን ዘለቀ ጋር ትዳር በመመሥረት አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ልጆችን ማፍራታቸዉን የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review