AMN- ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም
እየተካሄደ በሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ እስከ አሁን የተወሰነ ነገር አለመኖሩን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) የምክከሩን የእስከ አሁን ሂደት በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም፣ ላለፉት ሁለት ቀናት አራት ሺህ ተሳታፊዎች በጥቃቅን ቡድን ተከፋፍለው (በ 50 ቡድን) አስር አስር በመሆን በተሰጣቸው አጀንዳዎች ላይ ሲመክሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የመከሩባቸው ጉዳዮችም፣ እየተሰነዱ መሆኑንና ተመካካሪዎች የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች በሚገባ እየተሰነዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪያው የምክከር ሂደት (የጥቃቅን ቡድን) ወደ ንዑስ ቡድን ተሻጋግሮ በሚገባ ምክክር እንደሚደረግም ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡
በምክክሩ ሁሉም ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እና በግልጽ እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸው እስከ አሁን ያለቀና የተወሰነ ነገር አለመኖሩን አብራርተዋል፡፡
ሀሳቦች እየተቀራረቡ ቢሆንም ነገር ግን ውሳኔ የሚቀርብበት ምዕራፍ ላይ ገና አልተደረሰም ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
የፊታችን ሰኞ የ250ዎቹ (ስልታዊ ቡድን) ምዕራፍ ተጠናቆ ወደ 500ዎቹ እንሸጋገራለን የሚል እምነት እንዳላቸውም ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ጠቁመዋል፡፡
ተመካካሪዎች ይህንን ታሪካዊ ሂደት በሚገባ እንዲጠቀሙበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የኮሚሽኑ ዓላማ ሁሉም በእኩልነት እንዲነጋገር መሆኑን ጠቁመውም የምክክሩ ሥነ-ዘዴ ሁሉም እኩል አሸናፊ ሆኖ አንዲወጣ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡