የካናዳ መንግስት የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀልና መልሶ የማቋቋም መርሃ ግብር እንዲሳካ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ

You are currently viewing የካናዳ መንግስት የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀልና መልሶ የማቋቋም መርሃ ግብር እንዲሳካ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ

AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም

የካናዳ መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀልና መልሶ የማቋቋም መርሀ ግብር በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚያደርገውን የገንዘብ፣ የቴክኒክና የስትራቴጂክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በኢትዮጵያ የካናዳ ልማት ትብብር ኃላፊ ሾን ቦይድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለውን የቀድሞ ተዋጊዎችን የመቀበል፣ ትጥቅ የመፍታት፣ የመመዝገብ፣ የማሰልጠን፣ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀልና መልሶ በማቋቋም (ዲዲአር) ሂደት የተመዘገቡ ውጤቶችንና እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ለካናዳው ልዑክ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እስካሁን 93 ሺህ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች በተሀድሶ ሂደት አልፈው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን ጠቅሰው እነዚህን ወገኖች በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ለፕሮግራሙ ስኬት ከለጋሽ ሀገራትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ካናዳ የዲ.ዲ.አር ፕሮግራሙ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የምታደርገውን ቁልፍ አጋርነት በማንሳት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የካናዳ ትብብር ኃላፊ ሾን ቦይድ በበኩላቸው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና የዲ.ዲ.አር ፕሮግራሙን በስኬት ለማጠናቀቅ የካናዳ መንግስት የሚያደርገውን የገንዘብ፣ የቴክኒክና የስትራቴጂክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በተለይም በሂደቱ አልፈው ወደ ማህበረሰቡ የተቀላቀሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ካናዳ በጽናት እንደምትደግፍ እና አጋርነቷ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከውይይት መድረኩ ጋር አያይዘው የካናዳ ልዑካን ቡድን አባላት ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ የDDR ትግበራ ሂደቶችን የሚያሳዩ የፎቶ ትዕይንቶችን መጎብኘታቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review