ለጅቡቲ የጭነት ተሽከርካሪዎች ተርሚናል ሊገነባ ነዉ

AMN ሐምሌ 23/2018

የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሞጆ ከተማ አስተዳደር ለጅቡቲ የጭነት ተሽከርካሪዎች ተርሚናል ግንባታ የተመደበውን መሬት በይፋ አስረክቧል።

በመሬት ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ( ዶ/ር) ፣ ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል ያለውን ጠንካራ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የሁለቱን ሀገራት የንግድና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች በማሻሻል የሕዝቦቻቸውን የጋራ ጥቅም እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀደም ሲል በጅቡቲ በነበራቸው ጉብኚት በተደረገው ውይይት መሠረት ላለፋት ሀያአምስት አመታት እልባት ሳያገኝ የቆየው ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በመጥቀስ ሚኒስትሩ አመስግነዋል ።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና የሞጆ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ለአመራራቸውና፣ ትብብራቸው እንዲሁም ላደረጉት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ( ዶ/ር) በማጠቃለያቸው፣ የጅቡቲ የጭነት ተሽከርካሪዎች ተርሚናል ግንባታ የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን በማዘመን፤ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንደሚያጠናክር፣ በቀጠናውም የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ብልጽግና ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በማስረከቢያ ሥነስርዓቱ ፣የጅቡቲ የመሠረተ ልማትና መሣሪያዎች ሚኒስትር ሐሰን ሁመድ ኢብራሂም ፣ የሞጆ ከተማ ከንቲባ እና ሌሎች የሁለቱ አገራት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ–ጅቡቲ ኮሪደር ለኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ዋነኛ መተላለፊያ በመሆኑ፣ ይህ ትብብር የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር እና ቀጣናዊ የንግድና የሎጂስቲክስ ትስስርን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያሸጋግር ተግባራዊ እርምጃ መሆኑ መጠቀሱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review