AMN ሐምሌ 23/2018

የኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ በተመካካሪዎች መካከል የመደማመጥና የጋራ መግባባት መንፈስን በማጠናከር በተሻለ አሳታፊነት እየተካሄደ መሆኑን የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበርና ተመካካሪ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋናው የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲሱ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በጉባኤውም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የወከሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች፣ በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እየተመካከሩ ይገኛሉ።
የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበርና ተመካካሪ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የመደማመጥና የመግባባት ባህልን በማጠናከር በተሻለ አሳታፊነት እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከአጀንዳ ማሰባሰብና ከተሳታፊዎች ልየታ ሂደት ጀምሮ አሳታፊነትንና አካታችነትን በተግባር በማረጋገጥ ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት ሕዝብን የወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በዋናው የምክክር ጉባኤ ላይ ሃሳባቸውን በነፃነት በማንሸራሸርና በግልጽ ተሳትፎ ተስፋ ሰጪ ምክክር እያካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤውም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀገራዊ ችግሮችን በሰለጠነ ምክክር ለመፍታት፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከርና ዘላቂ የሆነ መግባባት ለመፍጠር የተገኘ ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገራዊ ምክክሩ የጋራ መግባባትን ለመፍጠርና በመፍትሔ ሃሳቦች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ በተመካካሪዎች መካከል ግልጽ፣ ነፃና አሳታፊ ምክክር እየተካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።
ጉባኤውም የሕዝብን የዘመናት ብሶት በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ በመስጠት ለሁሉም የሚበጅ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነባ ታሪካዊ እርሾ መሆኑን ገልጸዋል።
የጋራ መግባባትን ለመገንባት የተፈጠረውን ይህን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ማሳሰባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።