የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የዜጎችን የባለቤትነት ስሜትና አብሮነት ያጠናከረ የሀገራዊ አንድነት ማሳያ ነው

You are currently viewing የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የዜጎችን የባለቤትነት ስሜትና አብሮነት ያጠናከረ የሀገራዊ አንድነት ማሳያ ነው

AMN – ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አረንጓዴ ሀገር ለመገንባት ያከናወነችው ዘርፈ ብዙ ተግባራት አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

ሀገሪቱ በየዓመቱ የምታካሂደውና አህጉራዊ ትኩረት የሳበው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ፣ የደን ሽፋንን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ረገድ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በመላው ሀገሪቱ በተከናወኑ ሰፊ የንቅናቄ ሥራዎች ታሪካዊ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን፤ እስካሁን በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የደን ሽፋን ከነበረበት 17 በመቶ ገደማ አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል።

ባለፉት ዓመታት በአንድ ቀን ብቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማስተባበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን የመተከል አበረታች ልምዶች የተመዘገቡ ሲሆን ፤ በ2017 ዓ.ም ብቻ ከ27 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በማሳተፍ በአንድ ጀምበር ከ714 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

በመርሃ ግብሩ ከዛፍ ዝርያዎች ባሻገር እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ የፍራፍሬ ዛፎች መካተታቸው የበርካታ አርሶ አደሮችን ኑሮ አሻሽሏል ፤ ኢትዮጵያንም በአፍሪካ ውስጥ ከአቮካዶ ላኪ ሀገራት ግንባር ቀደም እንድትሆን አስችሏታል።

የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሃሳብ ለሚከናወነው የዘንድሮው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከቀድሞዎቹ የላቀ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ለዚህም ስኬት የሚተከሉ ችግኞች እና የጉድጓድ ቁፋሮ እንዲሁም ሕዝባዊ ተሳትፎን ማቀናጀት የሚያስችሉ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።

በዘንድሮው መርኃ ግብር አካባቢ ስነ-ምህዳር ተስማሚ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከ8 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተው ነው እየተተከሉ የሚገኙት።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አረንጓዴ ሀገር ለመገንባት ያደረገችው ይህ ጉዞ፣ የዜጎችን የባለቤትነት ስሜትና አብሮነት ያጠናከረ ታላቅ ሀገራዊ ማሳያ ሆኖ ቀጥሏል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review