AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

ሀገራዊ ራዕያችንን ለማሳካትና ዘላቂነት ያለው መጻኢ ዕድል ለመፍጠር ወጣት ኃይላችንን በዕውቀት፣ በፈጠራና በአመራር ብቃት እየገነባን ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “አረንጓዴ አሻራ ለዘለቄታዊ የግብርና ልማትና አረንጓዴ ኢኖቬሽን” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀውን 6ኛውን ዓመታዊ የወጣቶች የአመራር ኮንፈረንስና የዲፕሎማሲ ጉባኤ አስጀምረናል ብለዋል ፡፡

የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማሳካት፣ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ተግተን በመነሳት፤ የሀገሪቱን የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ዘርፍ የማዘመን፣ የምግብ ዋስትናንና ብሔራዊ ክብርን የማረጋገጥ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለንም ነው ያሉት፡፡
ይህንን ሀገራዊ ራዕይ ይበልጥ ለማሳካት ዋነኛ አቅማችን የሆነውን ወጣት ኃይላችንን በዕውቀት፣ በፈጠራና በአመራር ብቃት እንዲገነባ እያደረግን ነውም ብለዋል፡፡

ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ኮንፈረንስ ወጣት መሪዎቻችን በምግብ ሉዓላዊነት፣ በአየር ንብረት መቋቋም እና በታዳሽ ኃይል ዙሪያ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦችንና አጋርነትን የሚፈጥሩበት እንዲሁም ለነገው ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ራሳቸውን በተግባር የሚያዘጋጁበት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ዛሬ በወጣቶቻችን ላይ የምናደርገው እያንዳንዱ ኢንቨስትመንት፣ ለምንገነባት የበለጸገች ሀገር ሁነኛ ዓምድ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ አረንጓዴ ዐሻራን እያኖርን የትውልዱን የለመለመ ተስፋ እየተከልን፣ አረንጓዴና ዘላቂ የሀገር ግንባታን ለማፋጠን እንትጋ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡