ኢትዮጵያ ላሳየችው አስደናቂ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅና በማግኘቷ ኮፕ 32 ጉባኤ የማስተናገድ ዕድል አግኝታለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ ላሳየችው አስደናቂ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅና በማግኘቷ ኮፕ 32 ጉባኤ የማስተናገድ ዕድል አግኝታለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት 800 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል ከማለዳው ጀምሮ መላው ሕዝቧን አስተባብራ ወደ ሥራ ገብታለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ይህ ጥረት ከወትሮው የተለየና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅናን ያተረፈ ታላቅ እንቅስቃሴ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩም የአፈር፣ የውኃ እና የተራሮቻችንን ደህንነት መጠበቅ የሀገራችን የወደፊት ዋስትና ነው ብለዋል።

ዛሬ የምንተክለው ዛፍ ለነገው ትውልድ ምግብ፣ ጥላ፣ ውበት እና የካርቦን ዘብ ይሆናል በማለትም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ላሳየችው አስደናቂ የአካባቢ ጥበቃ ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅና በማግኘቷ፣ ከ80 ሺህ እስከ 100 ሺህ ተሳታፊዎች እና ከ100 በላይ የሀገር መሪዎች የሚታደሙበት ታላቁ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 32) በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ተወስኗል ብለዋል።

ይህ ጉባኤ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰሃራ በታች ባለ ሀገር የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ያደገችና ተስፋ ያላትን ኢትዮጵያ ለዓለም ለማሳየት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

ንቁ፣ አሳታፊ እና አስተማማኝ መሠረት በመጣል የጸናች ሀገር መገንባት የሚቻለው በጋራ ጥረት ብቻ ነው በማለትም አክለዋል።

ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መላው ኢትዮጵያውያን በጀመርነው መንገድ ተባብረን በመቀጠል የያዝነውን ግብ እናሳካለን ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review