AMN- ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል።
አቶ አደም ፋራህ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፣ ዘንድሮ የሚከናወነው ተግባር ባለፈው ዓመት የተመዘገበውን የ714 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ ክብረ ወሰን በማሻሻል ለነገዋ የበለጸገች ሀገር አረንጓዴ መሰረት የሚጥል ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ነው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በ2011 ዓ.ም ሲጀመር፣ ዋና መነሻው የኢትዮጵያን የተወሳሰቡ የስነ-ምህዳር እና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ እንደነበር አቶ አደም አብራርተዋል።
ደን ሲጨፈጨፍ አፈር እንደሚሸረሸር፣ የውሃ ምንጮች እንደሚደርቁ እና የግብርና ምርታማነት በመቀነሱ ለስራ አጥነት፣ ለምግብ ዋስትና እጦት፣ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪና ለሉዓላዊነት ስጋት እንደሚዳርግ የጠቆሙት ኃላፊው፤ መርሃ ግብሩ ይህንን የተሳሰረ የችግር አዙሪት ለመበጠስ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ 48 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
በዚህም እንደ አቮካዶና ቡና ያሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዋጋ ያላቸው ተክሎች በመተከላቸው የውጭ ምንዛሬ ግኝት አድጓል፣ የደን ሽፋን እየጨመረ፣ የስነ-ምህዳር ደህንነት እየተጠበቀ እና የውሃ አካላት እየታደሱ ይገኛሉ ብለዋል።
በበረከት ጌታቸው