AMN ሐምሌ 27/2018
የሀገር ዳር ድንበር እያስከበርን ለትውልድ የሚሻገር አሻራችንን በጋራ አኑረናል ሲሉ የሰሜን ምሰራቅ ዕዝ አመራርና አባላት ተናገሩ።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምሰራቅ ዕዝ አመራርና አባላት “ተስፋን እንትከል”በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ባለው የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።
የሰሜን ምሰራቅ ዕዝ ፋይናንስ ስራ መሪ ኮሎኔል ብርሃን ጥላዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመከላከያ ሰራዊት አገራዊ ተልዕኮውን ከመወጣት ባለፈ በተለያዮ የልማት ተግባራት ላይ እየተሳተፈ ይገኛል ።
በተለይም ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ እያስገኘ በመሆኑና ለትውልድ የሚሻረር ተግባር በመሆኑ የድርሻቸው እየተወጡ መሆኑን አብራርተዋል።
የሰሜን ምሰራቅ ዕዝ የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሻለቃ ፀጋዬ ገብሬ በበኩላቸው፤ የመከላከያ ስራዊት በየትኛውም የሀገሪቱ ዳርቻ የህዝብ አጋርነቱን በማሳየት ግዳጁን እየተወጣ ነው።
የአገርን ዳር ድንበር ከማሰከበር ጎን ለጎንም ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በሚያሰገኝ የልማት ስራ ላይ አሻራቸውን እያሳረፉ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
በመርሃ ግብሩ ላይ በመሳተፍ አሻራቸውን ያኖሩት ምክትል መቶ ዓለቃ ሃና ተካ ፤ ስራዊቱ ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ስራዎች በመሳተፍ የህዝብ አጋርነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመሳተፍም ሀገሪቱ የያዘችውን የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ስራ በማገዝ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ነው የገለጹት።
መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋምና ለመቀነስ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በችግኝ ተከላው ላይ አሻራቸውን ማኖራቸውን የገለጹት ደግሞ ምክትል አሰር ዓለቃ መሐመድ ዛኪር ናቸው።