AMN – ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

በመላው ኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ላይ እስከ ቀኑ 9፡00 ሰዓት ድረስ ብቻ 700 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ አስታወቁ።
ሚኒስትሯ የዕለቱን የችግኝ ተከላ አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያውያን የያዙትን 800 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር የመትከል ሀገራዊ ግብ ለማሳካት በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት እና ንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህም መሠረት ከማለዳው ጀምሮ እስከ ቀኑ 9፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ 22 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች በዕለቱ መርሃ ግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል ነው ያሉት።
በቀሪዎቹ ሰዓታት መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፣ አጠቃላይ የዕለቱ የችግኝ ተከላ የዋና አፈጻጸም መረጃዎች በቀጣይ ተጠናቅረው ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ይጠበቃል።
በፍሬህይወት ብርሃኑ