AMN – ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም
ዓላማዋ ግልጽ ኅልሟም ትልቅ ነውና ወዲህ የክረምቱ ቅዝቃዜ ወዲያም የበጋው ሐሩር ደግሞም የጎዳናው ወከባ አልበገራትም።
ቦሌ አራብሳ በተለምዶ 15 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ጎዳና ዳር ቁጭ ብላ በብሩሾቿ የሥዕል ጥበብ የምትፈጥረው የ17 ዓመቷ ማርያማዊት ሲሳይ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ናት።
ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረገችው ቆይታ ፣ ሥዕልን በቻርት ወረቀትና በእርሳስ እንደጀመረች ታወሳለች።
ዛሬ ጎዳና ዳር ሆና የምትሥላቸው ሥዕሎች ቀልብን ይገዛሉ፤ ዐይንንም ይይዛሉ።
ከትምህርቷ ጎን ለጎን የምትሥላቸውን ሥዕሎች በመሸጥ እናቷን ትደጉማለች ፤ ዕድሜዋም ሁኔታውም አታልሏት ቅድሚያ ለኔ አላለችም።
ለእናቷ ለግሣ የተረፋትን ተማሪም ሴትም ናትና የሚያስፈልጋትን ለማሟላት ትጥራለች።

በዚህ ዕድሜ ጎዳና ላይ ሆኖ መሥራት ፈተናው ቀላል ባይሆንም፤ ዝቅ ካላሉ ከፍ ማለት የለምና ተስፋን እንጅ ችግርን ዐላይም ትላለች።
ብላቴናዋ መንፈሰ ጠንካራ ሠዓሊ ማርያማዊት፤ የምትሠራበት ስቱዲዮና ምቹ ቦታ የላትም።
ቤተሰብ በቀለም ሽታ እንዳይረበሽ በማሰብም፤ ለዝናብ፣ ቅዝቃዜ እና ፀሐይ እጅ ሳትሰጥ ሥራዎቿን በሙሉ ጎዳና ላይ ቁጭ ብላ ትከውናለች።
ጀማሪ ሠዓሊ ናትና ብዙም ገቢ ባለመኖሩ የቀለም፣ የብሩሽ እና ሸራ እጥረትም ይፈትናታል።
ቢሆንም እናቷን ለመደጎም የራሷን ወጪም ለመሸፈን ሥራ መቆም የለበትምና፤ ጊዜ ጥንካሬያቸውን በነፈጋቸው ብሩሾች ቀለም እየቧጠጠች ትሥላለች።
ማንን እንደምታደንቅ በተጠየቀች ጊዜም ፤ ዓለም ያከበራቸውን የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ስትል መልሳለች።
ተፈጥሮ አንዱን ስታስቀድም ሌላኛውን ማዘግየቷ እንጂ ፤ አግኝታ አድናቆቷንም ሐሳቧንም ብታጋራቸው ምኞቷ መሆኑን አንስታለች።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ፣ አርቲስት ጥላሁን ገሰሰን እና የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች የትነበርሽ ንጉሤን ጨምሮ ታዋቂ ሰዎችን ሥላ በዐውደ ርዕይ የማቅረብ ፍላጎት እንዳላትም ጠቁማለች።
ወጣትነት ፈታኝ የዕድሜ ክልል መሆኑን በማስረዳት፤ ወጣቶች ከስሜታዊነት ርቀው ነገን በማሰብ ዓላማቸውን ማሳካት እንዳለባቸውም ትመክራለች።
በታምራት ቢሻው