በቴክኖሎጂ የታጀበው ችግኝ ቆጠራ

You are currently viewing በቴክኖሎጂ የታጀበው ችግኝ ቆጠራ

AMN – ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ትናንት በአንድ ጀምበር ችግኞችን ስትተክል የሂደቱን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች፣ የጂኦስፓሻል መረጃዎች እና ሣይንሳዊ የቁጥጥር ማዕቀፎች ሥራ ላይ ውለዋል።

የችግኝ ቆጠራ እና ማረጋገጫ ሂደቱ የተጀመረው ከ130 ሺህ ከሚልቁ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የሚወጡትን ችግኞች ሥርጭት በመመዝገብ ነበር፡፡

በየቀበሌው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም በሞባይል መተግበሪያዎች አማካኝነት የተተከሉትን ችግኞች ብዛት ወደ ማዕከላዊ የክትትል ማዕከል ሲያስገቡ ውለዋል።

ወደ ማዕከሉ የገቡ መረጃዎችም ቀድሞ ከተለዩት የመትከያ ቦታዎች እና ችግኝ የማስተናገድ ዐቅማቸው ጋር ተመሳክረው ትክክለኛነታቸው የታወቀ ሲሆን፤ በዚህም 805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸው ተረጋግጧል፡፡

የተተከሉት ችግኞች እስከሚፀድቁ ክትትል የሚደረግ ሲሆን፤ እያንዳንዱ የመትከያ ቦታ በጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ ዲጂታላይዝ ተደርጎ ትክክለኛ የችግኝ መገኛ ጣቢያው፣ የችግኙ ዓይነት እና የተተከለበት ቀን በመረጃ ቋት ውስጥ እንዲመዘገብ ተደርጓል።

እንዲሁም ችግኞቹ ከተተከሉ በኋላ በ30ኛው ቀን ከመሬቱ ጋር መዋኀዳቸውን፣ በ90ኛው ቀን ሥር መስደዳቸውን እና በ180ኛው ቀን የበጋውን ወራት የመቋቋም ዐቅማቸውን ለመገምገም ኦዲት የሚደረግ ይሆናል፡፡

የችግኞቹ ማደግ እና የደን ሽፋኑ መጨመር በሳተላይት ምስሎች እና በእፅዋት አረንጓዴነት አመልካች ትንተናዎች አማካኝነት ይረጋገጣል።

ይህ ሁሉ አጠቃላይ መረጃ ተጠናቅሮ በዓለም ባንክ የካርቦን ብድር ሥርዓት በኩል ገለልተኛ የሦስተኛ ወገን ማረጋገጫ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

በዚሁ የተቀናጀ እና ሣይንሳዊ አሠራር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የትኩረት ማዕከል የሆነውን የአረንጓዴ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዋን በቁርጠኝነት እያረጋገጠች ትገኛለች።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review